Latest News

Bahir Dar University - Bahir Dar Institute of Technology (BiT) hosts a consultative workshop on Research, Innovation & Technology Transfer to Meet the National Agenda

To view the news, please visit: https://www.facebook.com/bitpoly/posts/1532562743811557

ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን የመስኖ እርሻ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው

*****************************************************************************

ባሕር ዳር፡- መጋቢት 3/2014ዓ/ም

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂ ምርቶችንና ዝርያዎችን በማላመድ የአርሶ አደሩን የመስኖ እርሻ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን ከሚሰራባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው የምዕራብ ጎጃም  ዞን ሰሜን ሜጫ  ወረዳ አዲስ ልደት  ቀበሌ የመስኖ  ስንዴ  ልማት ጉብኝት መርኃ ግብር መጋቢት 03/2014 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

 

በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሀፊ ዶ/ር አስማረ ደጀን እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲዎች በአገራችን ብሎም በክልላችን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ እየሰሩ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሄክታር በላይ የስንዴ ልማት አልምተዋል፡፡ በመሆኑም በክልሉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በሻገር የዘር ብዜትን ለማሳደግ የመስኖ ስንዴ ልማት ላይ በስፋት መስራት እንደሚገባ ዶ/ር አስማረ ደጀን ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት የመስኖ ስንዴ ልማቱ ከአሁን በፊት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር፤ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደድር እና አርሶ አደሮችን ጨምሮ በሦስት የተለያዩ ጊዜያት መጎብኘቱን ገልጸው የዛሬው ጉብኝት በአማራ ክልል ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ አመራሮችና ተመራማሪዎች የተሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የግብርና ኮሌጅ ድህረ-ምረቃ ምርምርና ማህበረሰብ  አገልግሎት ምክትል  ዲን ዶ/ር ተስፋዬ መላክ እንደገለጹት የመስኖ ስንዴ ልማቱ እየተሰራ ያለው በምዕራብ ጎጃም  ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ  በሚገኙት የአዲስ ልደትና አዲስ አለም ቀበሌዎች እንዲሁም ናዳ ማሪያም ላይ ሲሆን በመስኖ ፕሮጀክቶች የሚለሙትን  የአርሶ አደር ማሳዎች  በዋናነት  እየተከታተሉ እንደሆነ ጠቁመው ከእቅዳቸው አኳያ በአዲስ ልደት ቀበሌ የመስኖ ልማት ከ650 እስከ 700 ሄክታር የሚደርስ የስንዴ ልማት በዩኒቨርሲቲው መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል። አክለውም ዶ/ር ተስፋዬ መላክ ከዚህ በፊት አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው ሳይሆን ያላቸውን ዘር በመጠቀም ብቻ ያመርቱ ስለነበር የሚያገኙት ምርት በጣም አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ከዚህ በፊት ስንዴ ያለሙ አርሶ አደሮች በሄክታር ከ18-20 ኩንታል ያገኙ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ከአንድ ሄክታር ከ40 እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ ለዚህም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ክትትልና ድጋፍ በማድረጋቸው የልማት ስራው ውጤታማ ሆኗል ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው የአማራ ክልል በዚህ አመት 80ሺህ ሄክታር ለማልማት አቅዶ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5,200 ሄክታሩን በምዕራብ ጎጃም ዞን ማልማት እንደተቻለ ገልጸው በቀጣይም አዳዲስ መሬቶችን በመለየት ሰፊ የውሃ አማራጮችን ተጠቅሞ ማልማት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከጎብኝዎች መካከል አንዷ የሆኑት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስካለማሪያም አዳሙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2014 ዓ.ም የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በማስፋት ወደ መሬት አውርደው ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ተንቀሳቅሰዋል ብለዋል፤ በዚህም ከ250 እስከ 500 ሄክታር እንዲያለሙ የታቀደውን በማልማት ውጤታማነታቸውን ባየነው የመስክ ጉብኝት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል ያለበት ተቋም በመሆኑ ከመማር ማስተማሩ ስራ በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራውን በማስፋት ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነትና ኑሮ መሻሻል የበኩሉን አስተዋፆ ማበርከት ይገባዋል፡፡

የግብርና መካናይዜሽንን በማስፋፋት የስንዴ ልማትን በማጠናከር ከርሃብ ስጋት ነጻ ለመሆንና የምርጥ ዘር አቅርቦትን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት መተካት ይቻል ዘንድ ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ዶ/ር አስካለማሪያም አዳሙ ተናግረዋል፡፡

አገራችን በቂ መሬትና ውሃ እያላት ዜጎቻችን የርሀብ ስጋት ሊጋረጥባቸው አይገባም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲም እየሰራ ያለው የስንዴ ልማት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ የሚሰጥና የሚያስደስት ነው፡፡

ጉብኝቱ ቀጥሎም በክልሉ የሚገኙ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ያለሙት የመስኖ ስንዴ ልማት እንደሚጎበኝ ተገልፆአል፡፡

 

በስነ ልቦና እና ስራ ፍለጋ ክህሎት ላይ ያተኮረ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጠ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ከዩኒቨርሲቲዉ የዉጤታማ ትግበራ ዳይሬክቶሬት ጋር በመተባበር
ከመጋቢት 01-02/2014 ዓ/ም በጥበብ ህንጻ አዳራሽ የአሰልጣኞች ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በአሰልጣኞች ስልጠና ከቢዚነስና ኢኮኖሚክስ ኮሌጅ፤ ከግብርናና አከባቢ ሳይንስ ኮሌጅ እና ከሳይንስ ኮሌጅ ለተመረጡ 26 መምህራን በስነ ልቦና እና የስራ ፍለጋ ክህሎት ስልጠና መሰጠቱን የዩኒቨርሲቲዉ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ወርቁ አበበ ገልፀውልናል፡፡

ስልጠናዉን ሲሰጡ ያገኘናቸዉ የዉጤታማ ትግባራ የስራ ተኮር አስተባባሪ ዮርዳኖስ ይበልጣል እንደገለጹት የስልጠናዉ ዓላማ ሰልጣኞች ከስልጠናው በኃላ በየኮሌጆቻቸዉ ለሚገኙ ተመራቂ ተማሪዎች የስነ-ልቦና ድጋፍ እንዲያደርጉ እና የስራ ፍለጋ መረጃ የመፈለግ ክህሎትን በማዳበር የመረጃ አፈላለግ ፤ ውሳኔ የመስጠት፤ የመደራደር ክህሎት፤ የተግባቦትና የትምህርት መረጃ አደረጃጀት ለምሳሌ የትምህርት ማመልከቻና የስራ ቃለ መጠየቅ ዝግጅት ክህሎት እንዲኖራቸው በማሰልጠን የማማከር ስራ እንዲሰሩ ያግዛቸዋል፡፡

በመጨረሻም  ከስልጠናው በቂ ዕዉቀት እንዳገኙና ለቀጣይ ስራቸዉም መነሳሳት የፈጠረላቸዉ መሆኑን በመግለጽ በቀጣይ መሰል ስልጠናዎች ለሌሎች መምህራንም እንዲሰጣቸዉ ሰልጣኞች አሳስበዋል፡፡

ዘጋቢ፡ወንዳለ ድረስ

 

በ2013 ዓ.ም.ለትምህርት ሚኒስቴር ያመለከቱና እውቅና የተሰጣቸው የሃገር ውሰጥ የምርምር ጆርናሎች

https://www.facebook.com/fdremoe/posts/330504609115613

ለዩኒቨርሲቲው የጥበቃና ደህንነት ሰራተኞች ስልጠና ተሰጠ

***************************************

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ሽግግርና ዩኒቨርሲቲ ኢንዱስትሪ ትስስር ዳይሬክቶሬት እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህራን አዘጋጂነት ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የጥበቃና ደህንነት ሰራተኞች በፈጣን የላፕቶፕ ባለቤትነት ማረጋገጫ ስርዓት(Fast digital verification system in Laptop’s ownership) ዙሪያ በስነ-ምድርና መረጃ ቴክኖሎጂ ማዕከል የስልጠና አዳራሽ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት መምህር የሆኑትና ስልጠናዉን የሰጡት  አቶ ሀብታሙ አለማየሁ ለሰልጣኞች በስልጠናው አስፈላጊነት ዙሪያ ገለፃ አድርገዋል፡፡ ይህ ቴክኖሎጂ የመረጃ አያያዝን እንደሚያዘምን፤ ጊዜና ጉልበትን እንደሚቆጥብ፤ ደህንነቱ የተረጋገጠ ፈጣን አገልግሎት መስጠት እንደሚያስችል፤ የመረጃ መጥፋትን፤ በወረቀቶች መቀደድና መጥፋት ምክንያት የሚደርስ የአገልግሎት ችግርን እንደሚቀርፍ አቶ ሀብታሙ ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም ይህ ቴክኖሎጂ ተአማኒ፣ ቀላልና ፈጣን በመሆኑ ለአጠቃቀም ምቹ እንደሆነ አቶ ሀብታሙ አለማየሁ ተናግረዋል፡፡

ፈጣን የባለቤትነት መለያ ስርዓት (Fast digital verification system customer’s property) የተሰኘዉ ይህ ቴክኖሎጂ በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች እንደሚሰራ የገለፁት አሰልጣኙ እነሱም የመረጃ ምዝገባ ስርዓት (QR Code Generator) እና የመረጃ ማረጋገጥ ስርዓት (Android Application) ይሰኛሉ ብለዋል፡፡

የስልጠናው ተሳታፊዎችም ስልጠናዉ አጭርና ግልፅ መሆኑን ገልፀው መሰል ስልጠናዎች በየጊዜው መዘጋጀታቸው የሰራተኛውን አቅም ያሳድጋል ብለዋል፡፡ ስልጠናዉ የተሰጠዉ ለአንድ ቀን ሲሆን 30 የጥበቃና ደህንነት ሰራተኞች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

 

Tibebe Ghion Specialized Hospital is offering second-round training on Laboratory Quality Management System to Tibebe Ghion Specialized Hospital laboratory professionals

For news in full: https://www.facebook.com/cmhsbdu/posts/1957502391118003

የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ መስጠት የሚያስችል ስልጠና ተሰጠ

*************************************************************

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስልጠና ዳይሬክቶሬት ከሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ጋር በመተባበር የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ስልጠና ከተማሪዎች መማክርት እና በጎ አድራጎት ክበባት ለተውጣጡ 60 ተማሪዎች ከመጋቢት 01- 02/2014 ዓ.ም ድረስ ለ2 ተከታታይ ቀናት  በቀድሞው ሴኔት የመሰብሰቢያ አዳራሽ የአሰልጣኞች ስልጠና እየተሰጠ ነው፡፡

በስልጠናው የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ የተማሪዎች መማክርት እና የበጎ አድራጎት ክበባት አባላት በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴያቸው የሚያስተውሉትን ድንገተኛ አደጋ፤ የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ ለመስጠት እና የጨበጡትን ዕውቀት ለህብረተሰቡ ለማካፈል ስልጠናውን ማግኘታቸው ፋይዳው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ በድንገተኛ እና ፅኑ ህሙማን ነርሲንግ ትምህርት ክፍል መምህር እየሩሳሌም ቃልዓብ እንደተናገሩት አብዛኛው ሰው የመጀመሪያ ህክምና እርዳታ አሰጣጥ ክህሎት ገና ጅምር ላይ በመሆኑ በክፍል ውስጥ ከምንሰጣቸው ትምህርት በተጨማሪ በተግባር የተደገፈ እውቀትን እንዲጨብጡ አልሞ የተዘጋጀ ስልጠና ነው ብለዋል፡፡

ሰልጣኞችም በዩኒቨርስቲ ቆይታቸው በማህበረሰቡ ዘንድ የሚያጋጥማቸውን የመጀመሪያ እርዳታ ፈላጊዎች በማንኛውም ቦታ መርዳት እንዲችሉ ሲሆን አንዳንዴ በሚከሰቱ አደጋዎች ላይ ባለማወቅ በተሳሳተ መንገድ ለመርዳት የሚሞክሩትን በማረም፤ ያገኙትን ክህሎት ለግቢ ተማሪዎችና ለሌሎችም የህብረተሰብ ክፍሎች ማካፈል እንደሚጠበቅባቸው መምህርት እየሩሳሌም ገልፀዋል፡፡

   ዘጋቢ፡- ወንዳለ ድረስ

 

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (March 08) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ተከበረ

**********************************************

(ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣የካቲት 30/2014 ዓ.ም)

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረው ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን “Marche 8” በተለያዩ ዝግጅቶች በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተከበረ፡፡

ዓለም አቀፉ የሴቶች ቀን (March 08) በዓልን ምክንያት በማድረግ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በዋናው ግቢ  የመሰብሰቢያ አዳራሽ  የፓናል ውይይት ተካሂዷል፡፡  በውይይቱ ላይ ዶ/ር ሙሉነሽ አበበ እና ዶ/ር አልማዝ ጊዜው እለቱን አስመልክተው ለተሳታፊዎች የሕይወት ልምድና ተሞክሯቸውን አካፍለዋል፡፡

በተካሄደው የፓናል ውይይት ላይ እለቱን አስመልክቶ ለውይይት መነሻ የሚሆን ጥናታዊ ጽሁፍ ቀርቦ በተሳታፊዎች ውይይት ተደርጎበታል፡፡ በፕሮግራሙ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘን  ጨምሮ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተሳትፈዋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ዘለቀ

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት  የአፍርካ ሻምፒዎን የብስክሌት ውድድር ተካሄደ

****************************************************

(ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣የካቲት 29/2014 ዓ.ም)

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን “March 8” በተለያዩ ዝግጅቶች በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እየተከበረ ነው፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንን (March 8) ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን እና ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 02/2014 ዓ.ም  ድረስ የሚቆይ ሀገር አቀፍ የአፍሪካ ሻምፒዎና የብስክሌት ማጣሪያ ውድድር “እኔ የህቴ ጠባቂ ነኝ ” በሚል መሪ-ቃል  በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ጊወርጊስ አደባባይ ተጀምሯል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ውድድሩን ያስጀመሩት የኢፌድሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር  የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ስፖርት አንድን ማህበረሰብ የማገናኘትና የማስተሳሰር እንደሀገር ከገባንበት ችግር የማውጣት እና ለሰላም የሚደረገውን ጉዞ የማፋጠን ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ታላቁ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምንም እንኳን በርካታ ስራዎች ቢኖሩበትም ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማገዝ እያደረገ ያለውን አስተዋፆ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስፖርቱ ዘርፍ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን እንደምሳሌ ወስደው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ በርካታ ወጣቶችን በውሃ ዋና፣ በአትሌቲክስ እና በብስክሌት ውድድሮች እየወጡ ያሉባት ከተማ በመሆኗ የዛሬው የአፍሪካ ሻምፒዎና የብስክሌት ማጣሪያ ውድድር መካሄዱ ወደፊት ለምናደርገው አህጉራዊ እና ሀገር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ  ሴቶች እንደ ወንዶች ጠቢባን እንደሆኑ የሚያሳይ የሀገር በቀል እውቀትና ተሞክሮ መኖሩንና እርሱም ተደብቆ በመኖሩ የተሳሳተ የነጭ ባህል የሆነውን ትርክት በትምህርት ስርዓቶቻችን አስገብተን ስለተማርን የተሳሳተ ግንዛቤ ህብረተሰባችን መያዙን ተናግረው ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንት ከነገስታቱ ጀምሮ የሀገርን ዳርድንበር በማስጠበቅና ጦር በመምራት ሴቶች ከፍተኛ ጥበብና ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ  በብስክሌት ታሪኳ ትታወቃለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህንን የቆዬ ባሕሏን ለመመለስ የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሆን ስፖርቱን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖንሰርነት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (March 08) ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሻምፒዎና የብስክሌት ማጣሪያ ውድድር ላይ ከአማራ ክልል፣ ከአዲስ አበባ፣ ከደቡብ ምዕራብ ክልል፣ ከሲዳማ ክልል እና ከድሬዳዋ ከተማ የተውጣጡ የብስክሌት ክለቦች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ዘለቀ

 

Pages