የአርሶ አደሩን የመስኖ እርሻ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ...

ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን የመስኖ እርሻ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሰራ ነው

*****************************************************************************

ባሕር ዳር፡- መጋቢት 3/2014ዓ/ም

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዳዲስ የግብርና ቴክኖሎጂ ምርቶችንና ዝርያዎችን በማላመድ የአርሶ አደሩን የመስኖ እርሻ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ስራዎችን ከሚሰራባቸው ቦታዎች አንዱ በሆነው የምዕራብ ጎጃም  ዞን ሰሜን ሜጫ  ወረዳ አዲስ ልደት  ቀበሌ የመስኖ  ስንዴ  ልማት ጉብኝት መርኃ ግብር መጋቢት 03/2014 ዓ.ም ተካሂዷል፡፡

 

በአማራ ክልል የሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ፎረም ዋና ጸሀፊ ዶ/ር አስማረ ደጀን እንደገለጹት ዩኒቨርሲቲዎች በአገራችን ብሎም በክልላችን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በአማራ ክልል ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች በመስኖ ስንዴ ልማት ላይ እየሰሩ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከሁለት ሺህ ስድስት መቶ ሄክታር በላይ የስንዴ ልማት አልምተዋል፡፡ በመሆኑም በክልሉ የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ በሻገር የዘር ብዜትን ለማሳደግ የመስኖ ስንዴ ልማት ላይ በስፋት መስራት እንደሚገባ ዶ/ር አስማረ ደጀን ተናግረዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የምርምርና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራው እንደገለጹት የመስኖ ስንዴ ልማቱ ከአሁን በፊት የግብርና ሚኒስቴር ሚኒስትር፤ የአማራ ክልል ርእሰ መስተዳደድር እና አርሶ አደሮችን ጨምሮ በሦስት የተለያዩ ጊዜያት መጎብኘቱን ገልጸው የዛሬው ጉብኝት በአማራ ክልል ከሚገኙ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተውጣጡ አመራሮችና ተመራማሪዎች የተሳተፉበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የግብርና ኮሌጅ ድህረ-ምረቃ ምርምርና ማህበረሰብ  አገልግሎት ምክትል  ዲን ዶ/ር ተስፋዬ መላክ እንደገለጹት የመስኖ ስንዴ ልማቱ እየተሰራ ያለው በምዕራብ ጎጃም  ዞን ሰሜን ሜጫ ወረዳ  በሚገኙት የአዲስ ልደትና አዲስ አለም ቀበሌዎች እንዲሁም ናዳ ማሪያም ላይ ሲሆን በመስኖ ፕሮጀክቶች የሚለሙትን  የአርሶ አደር ማሳዎች  በዋናነት  እየተከታተሉ እንደሆነ ጠቁመው ከእቅዳቸው አኳያ በአዲስ ልደት ቀበሌ የመስኖ ልማት ከ650 እስከ 700 ሄክታር የሚደርስ የስንዴ ልማት በዩኒቨርሲቲው መሸፈን መቻሉን ገልጸዋል። አክለውም ዶ/ር ተስፋዬ መላክ ከዚህ በፊት አርሶ አደሮች ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ ተጠቅመው ሳይሆን ያላቸውን ዘር በመጠቀም ብቻ ያመርቱ ስለነበር የሚያገኙት ምርት በጣም አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ከዚህ በፊት ስንዴ ያለሙ አርሶ አደሮች በሄክታር ከ18-20 ኩንታል ያገኙ የነበረ ሲሆን ዘንድሮ ግን ከአንድ ሄክታር ከ40 እስከ 50 ኩንታል ምርት እንደሚገኝ የተደረጉ ጥናቶች ያመለክታሉ ለዚህም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች ክትትልና ድጋፍ በማድረጋቸው የልማት ስራው ውጤታማ ሆኗል ብለዋል ዶ/ር ተስፋዬ፡፡

የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ቃልኪዳን ሽፈራው በበኩላቸው የአማራ ክልል በዚህ አመት 80ሺህ ሄክታር ለማልማት አቅዶ የነበረ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 5,200 ሄክታሩን በምዕራብ ጎጃም ዞን ማልማት እንደተቻለ ገልጸው በቀጣይም አዳዲስ መሬቶችን በመለየት ሰፊ የውሃ አማራጮችን ተጠቅሞ ማልማት ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ከጎብኝዎች መካከል አንዷ የሆኑት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስካለማሪያም አዳሙ ዩኒቨርሲቲዎች በ2014 ዓ.ም የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራን በማስፋት ወደ መሬት አውርደው ተጨባጭ ውጤት ለማምጣት ተንቀሳቅሰዋል ብለዋል፤ በዚህም ከ250 እስከ 500 ሄክታር እንዲያለሙ የታቀደውን በማልማት ውጤታማነታቸውን ባየነው የመስክ ጉብኝት ማረጋገጥ ተችሏል ብለዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲ ብዙ የተማረ የሰው ኃይል ያለበት ተቋም በመሆኑ ከመማር ማስተማሩ ስራ በተጨማሪ የማህበረሰብ አገልግሎት ስራውን በማስፋት ለማህበረሰቡ ተጠቃሚነትና ኑሮ መሻሻል የበኩሉን አስተዋፆ ማበርከት ይገባዋል፡፡

የግብርና መካናይዜሽንን በማስፋፋት የስንዴ ልማትን በማጠናከር ከርሃብ ስጋት ነጻ ለመሆንና የምርጥ ዘር አቅርቦትን በበቂ ሁኔታ ለማግኘት እንዲሁም በውጭ ምንዛሬ የሚገባውን ስንዴ በአገር ውስጥ ምርት መተካት ይቻል ዘንድ ዩኒቨርሲቲዎች በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ዶ/ር አስካለማሪያም አዳሙ ተናግረዋል፡፡

አገራችን በቂ መሬትና ውሃ እያላት ዜጎቻችን የርሀብ ስጋት ሊጋረጥባቸው አይገባም የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲም እየሰራ ያለው የስንዴ ልማት ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ተሞክሮ የሚሰጥና የሚያስደስት ነው፡፡

ጉብኝቱ ቀጥሎም በክልሉ የሚገኙ ስድስት ዩኒቨርሲቲዎች ያለሙት የመስኖ ስንዴ ልማት እንደሚጎበኝ ተገልፆአል፡፡