የአፍርካ ሻምፒዎን የብስክሌት ውድድር

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት  የአፍርካ ሻምፒዎን የብስክሌት ውድድር ተካሄደ

****************************************************

(ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣የካቲት 29/2014 ዓ.ም)

በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ111ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ46ኛ ጊዜ የሚከበረውን ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀን “March 8” በተለያዩ ዝግጅቶች በባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ እየተከበረ ነው፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዓለምአቀፍ የሴቶች ቀንን (March 8) ምክንያት በማድረግ ከኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን እና ከባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ጋር በመተባበር ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 02/2014 ዓ.ም  ድረስ የሚቆይ ሀገር አቀፍ የአፍሪካ ሻምፒዎና የብስክሌት ማጣሪያ ውድድር “እኔ የህቴ ጠባቂ ነኝ ” በሚል መሪ-ቃል  በዛሬው ዕለት በባሕር ዳር ከተማ ጊወርጊስ አደባባይ ተጀምሯል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ውድድሩን ያስጀመሩት የኢፌድሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር  የስፖርት ልማት ዘርፍ ሚንስትር ዴኤታ አምባሳደር መስፍን ቸርነት ስፖርት አንድን ማህበረሰብ የማገናኘትና የማስተሳሰር እንደሀገር ከገባንበት ችግር የማውጣት እና ለሰላም የሚደረገውን ጉዞ የማፋጠን ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ታላቁ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምንም እንኳን በርካታ ስራዎች ቢኖሩበትም ከመማር ማስተማር ስራው ጎን ለጎን ህብረተሰቡን የሚጠቅሙ ስፖርታዊ ውድድሮችን በማገዝ እያደረገ ያለውን አስተዋፆ ሌሎች የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስፖርቱ ዘርፍ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን እንደምሳሌ ወስደው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ በርካታ ወጣቶችን በውሃ ዋና፣ በአትሌቲክስ እና በብስክሌት ውድድሮች እየወጡ ያሉባት ከተማ በመሆኗ የዛሬው የአፍሪካ ሻምፒዎና የብስክሌት ማጣሪያ ውድድር መካሄዱ ወደፊት ለምናደርገው አህጉራዊ እና ሀገር አቀፍ ስፖርታዊ ውድድሮች ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አምባሳደር መስፍን ቸርነት ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት  የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ  ሴቶች እንደ ወንዶች ጠቢባን እንደሆኑ የሚያሳይ የሀገር በቀል እውቀትና ተሞክሮ መኖሩንና እርሱም ተደብቆ በመኖሩ የተሳሳተ የነጭ ባህል የሆነውን ትርክት በትምህርት ስርዓቶቻችን አስገብተን ስለተማርን የተሳሳተ ግንዛቤ ህብረተሰባችን መያዙን ተናግረው ሀገራችን ኢትዮጵያ ጥንት ከነገስታቱ ጀምሮ የሀገርን ዳርድንበር በማስጠበቅና ጦር በመምራት ሴቶች ከፍተኛ ጥበብና ሚና እንደነበራቸው ገልጸዋል፡፡ የባሕር ዳር ከተማ  በብስክሌት ታሪኳ ትታወቃለች ያሉት ፕሬዚዳንቱ ይህንን የቆዬ ባሕሏን ለመመለስ የባሕር ዳር  ዩኒቨርሲቲ ከከተማው አስተዳደር ጋር በመሆን ስፖርቱን የሚያጠናክሩ ስራዎች እየተሰሩ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖንሰርነት ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀንን (March 08) ምክንያት በማድረግ እየተካሄደ ባለው የአፍሪካ ሻምፒዎና የብስክሌት ማጣሪያ ውድድር ላይ ከአማራ ክልል፣ ከአዲስ አበባ፣ ከደቡብ ምዕራብ ክልል፣ ከሲዳማ ክልል እና ከድሬዳዋ ከተማ የተውጣጡ የብስክሌት ክለቦች መሳተፋቸው ታውቋል፡፡

ዘጋቢ፡- ሙሉጌታ ዘለቀ