ለአንድ ወር ከ15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ስፖርታዊ ውድድር ተጠናቀቀ
**********************************************************
[ግንቦት 24/2014ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ]
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከባሕር ዳር ከተማ ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር ጋር በመተባበር በታራሚዎች እና ፖሊስ አባላት መካከል ለአንድ ወር ከ15 ቀናት ሲካሄድ የነበረው ስፖርታዊ ውድድር ፍጻሜ በሰባታሚት ማረሚያ ቤት ግቢ በሚገኘው የስፖርት ሜዳ በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች እና ሽልማቶችን በማበርከት ተጠናቀቀ።
የባሕር ዳር ማረሚያ ቤት መምሪያ ኃላፊ ኮማንደር አበርሃም ተስፋዬ የዚህ ስፖርታዊ ውድድር ዓላማ በታራሚዎች መካከል የእርስ በርስ ግንኙነት እንዲሁም ከፖሊስ አባላት ጋር ያለውን መልካም ግንኙነት የበለጠ ለማጠናከር፣ ሁሉም የህግ ታራሚዎች ከሌሎች መሰረታዊ የሙያ ስልጠናዎችና የቀለም ትምህርት ባለፈ የማረሚያ ቤት ቆይታቸውን በስፖርት እንቅስቃሴ በማሳለፍ በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና እንዲታነጹ እንዲሁም በስፖርት እንዲዝናኑ ማድረግ የመጀመሪያው ዓላማ ሲሆን ሁለተኛው ጥሩ የስፖርት ችሎታ ያላቸውን ታራሚዎች እና አባላትን በመለየት ተቋሙን የሚወክል ጠንካራ ቡድን ማፍራት ነው። እነዚህን ዓላማዎች ከሞላ ጎደል አሳክተናል ማለት እንችላለን ብለዋል።
ኮማንደር አበርሃም አክለውም በቀጣይ ይህን መልካም ጅምር በርካታ ታራሚዎችን በስሜት እና በሞራል ያዝናና፣ ያስደሰተ መሆኑን ስለተረዳን ተቋሙ የራሱን አቅም በመጠቀም እና ስፖርቱን ሊደግፉ የሚችሉ መንግስታዊ እና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን በማፈላለግ፣ የስፖርት ግባቶችን በማሟላት ቀጣይነት እንዲኖረው በጋራ እንሰራለን ብለዋል። በተጨማሪም ከህግ ታራሚዎች የሚጠበቀው እንዳሳለፍነው የውድድር ወቅት መልካም ስነ-ምግባር መሆኑን ጠቁመው የተለያዩ ድርጅቶችም ስፖርቱን ከመደገፍ አኳያ ላደረጉት የገንዘብ፣ የጉልበት እና የሞራል አስተዋፅኦ ምስጋና በማቅረብ በቀጣይም ለሚከናወኑ የማረምና ማነፅ ተግባራት ሁሉ ቅን ተሳታፊ እንዲሆኑ ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡
የአብክመ ማረሚያ ቤቶች ኮሚሽን የህግ ታራሚዎች ማረምና ማነጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ያዜ መኮንን በበኩላቸው “ይህ ውድድር ለስነ-ልቦና፣ ለአካል እና ለጤና አዎንታዊ አስተዋፅኦ ከማድረግ በተጨማሪ በታራሚዎች፤ በአባላትና በተቋማት እንዲሁም በግለሰብ ደረጃ ያለውን የእርስ በርስ ጤናማ የሆነ ግንኙነት የሚያጠናክር ሲሆን ለወደፊትም ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል፡፡
ስፖርታዊ ውድድሩ የተካሄደው በታራሚዎች እና በፖሊስ አባላት መካከል ሲሆን የተካሄዱት የስፖርት አይነቶችም እግር ኳስ፣ ገመድ ጉተታ፣ ሩጫ እና መረብ ኳስ ሲሆኑ በእያንዳንዱ የስፖርት አይነት አሸናፊ ለሆኑ ቡድኖች የዋንጫ፣ የሜዳሊያ እና የማበረታቻ ሽልማት ተሰጥቷል፡፡ ለአስተባባሪዎችና ድጋፍ ላደረጉ የቤንማስ እና አዲስ አምባ ሆቴሎች እንዲሁም ግለሰቦች የምስጋና እና የምስክር ወረቀት በዝግጅቱ ላይ በተገኙ ተጋባዥ እንግዶች ተበርክቶላቸዋል።
የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የስፖርት አካዳሚ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን ዶ/ር ተከተል አብርሃም “በየዓመቱ የውስጥ ውድድር ከመካሄዱ በፊት ሁሉንም ታራሚዎች የአካል ብቃታቸውን እና የሥነ-ልቦና አቅማቸውን ለማጎልበት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ መምህራን አጫጭር ስልጠናዎችን በመስጠት ከማረሚያ ቤቶች ጋር በመተባበር ቀጣይነት እንዲኖረው ይደረጋል ብለዋል።
ዶ/ር ተከተል አያይዘውም ሌሎች መንግስታዊም ሆኑ መንግስታዊ ያልሆኑ ባለድርሻ አካላትና ደርጅቶች ለታራሚዎች የበኩላቸውን ድጋፍ እና እስተዋጽኦ በማድረግ የዜግነታቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ መልዕክት አስተላልፈዋል።
ዘጋቢ፡- ባንቹ ታረቀኝ