የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ ያገኙ 5 መምህራን እና ተመራማሪዎች የህይወት ልምዳቸውን አካፈሉ
************************************************************************
(ሰኔ 17/2014 ዓ/ም፤ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በያዝነው ዓመት የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እድገት የተቀበሉ አምስት አንጋፋ ምሁራን የህይወት ልምዳቸውን ያካፈሉበት መርሃ-ግብር የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚዳንት ጨምሮ በርካታ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና ተማሪዎች በተገኙበት ሰኔ 17/2014 ዓ.ም በቀድሞው ሴነት አዳራሽ ተካሂዷል፡፡
መርሃ-ግብሩ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ በቶሌ ቀበሌ የተጨፈጨፉ ንፁኋን የአማራ ተወላጆችን በማሰብ የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማድረግ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በተገኙበት ተጀምሯል፡፡ ፕሬዚዳንቱ በንግግራቸው የሙሉ ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እድገት የተሰጣቸው አንጋፋ መምህራን እና ተመራማሪዎችን የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዶ/ር ፍሬው አክለውም በፕሮፌሰርነት ማዕረግ ማደግ በብዙ መልኩ የዩኒቨርሲቲውም እድገት እንደሆነ ተናግረው፤ የፕሮፌሰር ማዕረግ እድገት ስትደርሱ ስራ የምትጀምሩበት ወቅት እንጅ ጡረታ የምትወጡበት ጊዜ ባለመሆኑ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እንደ አንድ የምርምር ዩኒቨርሲቲ የበሰሉ እና ጠንካራ ጥናቶችን ከመስራትም ባለፈ ያገኛችሁትን እድገት ተጠቅማችሁ የበለጠ ወደ ማህበረሰቡ እንድትቀርቡና የማህበረሰቡን ችግር የሚፈቱ የመፍትሄ ሀሳቦችን ከማመንጨት አንፃር ዩኒቨርሲቲው ከእናንተ ብዙ ይጠብቃል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በመርሃ-ግብሩ እንደተገለፀው በቆዳ ህክምና (Dermatovenerology) ፕሮፌሰር ወንድማገኝ እምቢያለ ከህክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ፣ በ Organic Chemistry ፕሮፌሰር አታክልት አበበ ከሳይንስ ኮሌጅ፣ በ Algebra ፕሮፌሰር ብርሃኑ አሳዬ ከሳይንስ ኮሌጅ፣ በሥርዓተ- ትምህርት እና መመሪያ (curriculum and instruction) ፕሮፌሰር ሰለሞን መለሰ ከትምህርትና ስነ-ባህሪ ሳይንስ ኮሌጅ እና በአካባቢ እና የተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር (Environment and Natural Resource management) ፕሮፌሰር አማረ ሰውነት ከማሕበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ የሙሉ ፕሮፈሰርነት ማዕረግ በማግኘታቸው የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ የሙያ ዘርፎች የፕሮፌሰሮችን ቁጥር ከ20 በላይ ማድረሱን ተከትሎ ወደፊት ጠንካራ የምርምር ዩኒቨርሲቲ ሆኖ ለመቀጠል አስተዋፆው የጎላ መሆኑ ተገልጿል።
እድገቱን ያገኙ ፕሮፌሰሮችም ለመርሃ-ግብሩ ተሳታፊዎች የህይወት ተሞክሮ እና ልምዳቸውን እንዲሁም በቆይታቸው ያሳተሟቸውን የምርምር ጽሁፎችን እና በወቅቱ ያጋጠሟቸውን ተግዳሮቶች በዶ/ር ማረው አለሙ መድረክ መሪነት አቅርበዋል፡፡ በቀረበው የህይወት ተሞክሮ እና ልምድ ላይ ተሳታፊዎች ጥያቄዎችን እና አስተያየቶችን አንስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ-BDU
ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ
Wisdom at the source of Blue Nile
Thank YOU for visiting and inviting our pages, for your likes and shares!
ለተጨማሪ መረጃዎች፡-
Telegram ፡- t.me/BDU_ISC_Official
Facebook: - https://www.facebook.com/bduethiopia
YouTube ፡- www.youtube.com/c/BduEduEt
LinkedIn ፡- www.linkedin.com/school/bahir-dar-university
Twitter: - https://twitter.com/bdueduet
Tiktok:- https://vm.tiktok.com/ZMLgRxdfL
website :- www.bdu.edu.et