የቴክስታይል ሳይንስ እና ምህንድስና ምርምር ማዕከል የመጀመሪያውን ሀገራዊ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡
Selam Campus
29 Dec, 2025
የቴክስታይል ሳይንስ እና ምህንድስና ምርምር ማዕከል የመጀመሪያውን ሀገራዊ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡
ታህሳስ 18/2018 ዓ.ም (BDU_EiTEX) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የቴክስታይል ሳይንስ እና ምህንድስና ምርምር ማዕከል "ለስነ-ምህዳርና አካባቢ ተስማሚ የሆኑ ለታቀደላቸው አገልግሎቶች የሚውሉ የቴክስታይል ውጤቶች ለዘላቂ እድገት" በሚል ርዕስ የመጀመሪያውን ሀገራዊ አውደ ጥናት አካሄደ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ በመክፈቻ ንግግራቸው ስለኢንስቲትዩቱ አመሰራረትና አሁን ሰለደረሰበት ደረጃ ገልጸው የዚህ አውደ ጥናት ዓላማ ሀገራችን በቴክስታይል ዘርፉ ከፍተኛ የሆነ አስተዋፅኦ ማድረግ የምትችል ብትሆንም እስካሁን ድርስ ግን የተለመዱ አልባሳትን ብቻ እያመረተች ስለሆነ ወደ ፊት ከአልባሳት በተጨማሪ ምን መስራት ይቻላል? የሚለውን ሀሳብ ለማስረጽ የታሰበ ነው ብለዋል፡፡
ቴክስታይል ለአልባሳት አገልግሎት የሚውል ሲሆን ከፋሽንነት በተጨማሪ ለህክምና አገልግሎት፣ ለአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ፣ ለአውሮፕላን ኢንዱስትሪው፣ ለኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው እንዲሁም በተለያዩ ኢንዳስትሪዎች ላይ ያገለግላል፡፡ ይህ አገልግሎት በሀገራችን በተፈለገው ልክ እያደገ ስላልሆነ ሀገሪቱ ወደ ኢንዱስትሪ መር እንቅስቃሴ እንድትገባ ለማድረግ የተቋቋመ አውደ ጥናት መሆኑንም ፕሮፌሰሩ ገልጸዋል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ ፖሊሲ አውጮች፣ የኢንዱስትሪ ባለሙያዎች ፤ ተጋባዥ እንግዶች ፤ የኢንስቲትዩቱ አመራሮች፣ መምህራን፣ እንዲሁም ተማሪዎች ተሳትፈዋል፡፡
ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች በመጡ ምሁራን ምርምሮች ቀርበው በታዳሚዎች ውይይት ተደርጎባቸዋል፡፡
በመጨረሻም የምርምር ጽሑፍ ላቀረቡት፣ ቁልፍ መልዕክት ላስተላለፉት፣ ፓናል ውይይት ላቀረቡት እንዲሁም ይህን ጉባኤ ላዘጋጁት ኮሚቴዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡
