ትምህርት ክፍሉ ለመጀመሪ ጊዜ የሚያስመርቃቸው የ3ኛ ዲግሪ እጩ ተመራቂዎች ተቋቁሞ
*******************************************************************
በሙሉጎጃም አንዱዓለም
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ በኢትዮጲያ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ የሆነውን በ3ኛ ዲግሪ የመጨረሻውን የጥናታዊ ጽሁፍ ተቋቁሞ ሀሙስ የካቲት 14፣2011 ዓ.ም. በደመቀ ሁኔታ አካሄደ፡፡
የፋኩልቲው አንጋፋ መምህርና ተመራማሪ ዶ/ር ማረው ዓለሙ ፕሮግራሙን በንግግር ሲከፍቱ እንደተናገሩት አገር በቀል በሆነው የአማርኛ ቋንቋ በ3ኛ ዲግሪ ደረጃ መሰራቱ ዋና ዓላማው ቋንቋውን ለማሳደግና ትምህርቱን ለማስፋፋት እንዲሁም የጥናት ዉጤቱ ለተለያዩ ሴክተር መስሪያ ቤቶች ግብዓት ለማድረግ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ዶ/ር ማረው አክለውም እርሳቸው በሚመሩት አማርኛን ማስተማር የ3ኛ ዲግሪ ፕሮግራም የሚጻፉ ጥናታዊ ጹህፎች ደረጃቸውንና ጥራታቸውን የጠበቁ ሆነው እንዲቀጥሉ ልዩ ትኩረት እንደሚሰጡ ተናግረዋል፡፡
የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ዳዊት አሞኘም ለተመዘገበው ስኬት በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉትን ሁሉንም በፋኩልቲው ስም አመስግነው የእለቱን አቅራቢ እንኳን ደስ አለህ በማለት በሶስት አመት ከመንፈቅ በሆነ ጊዜ ብቻ ፕሮግራሙን ለማጠናቀቅ መቻሉ በራሱ ትልቅ ስኬት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ምናልባትም በዚህ አጭር ጊዜ ሲጠናቀቅ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ የመጀመሪያው ሊሆን እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡
የአሁኑ እጩ ተመራቂዎች በፋኩልቲው ስር የኢትዮጲያ ቋንቋዎችና ስነ-ፅሁፍ መምህር የሆኑት አቶ ማስተዋል ውበቱ እና የዓርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ሐይላኣይ ተስፋይ ሲሆኑ በዕለቱ ጥናታቸውን ያቀረቡት አቶ ማስተዋል የጥናታቸው ርዕስ “ የትብብር ብልሀታዊ ማንበብ ዘዴ” የተሰኘ ነው፡፡ ለጥናቱ መነሻ የሆነው ከ1-8 ክፍል ያሉ ተማሪዎች የማንበብ ልምዳቸውና ተነሳሽነታቸው አናሳ መሆኑንን የሚጠቁሙ ጥናቶች መኖራቸው እና የ1ለ5 የትብብር ብልሀትም በአግባቡ አለመተግበሩ እንደሆነ አቅራቢው ጠቁመው ጥናታቸውም የተጠቀሰውን የንባብ ብልሀት ለመፈተሸ ያለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እጩ ተመራቂው ስለ ስለጥናታቸው ለሰላሳ ደቂቃ ያህል ካቀረቡ በኋላ ከውጭ እና ከውስጥ ለመጡ ገምጋሚዎች እንዲሁም ከታዳሚው ለተነሱ አጠቃላይ ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ በመጨረሻም የእለቱ ሊቀመንበር የክፍቱ ተቋቁሞ እንደተጠናቀቀ ገልጸው ተቋቁሞው ከ15 ደቂቃ ረፍት በኋላ በዝግ እንደሚቀጥል በማመልከት ለነበረው ጊዜ ታዳሚውን አመስግነዋል፡፡