አካዳሚው ለዕርዳታ ማዕከሉ ድጋፍ ሰጠ

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ተስፋ የህፃናትና አረጋዊያን መርጃ ማእከልን ጎበኙ!!
 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ተማሪዎች በተስፋ የማህበረሰብ አቀፍ ልማት ማህበር ማዕከል ጥር 25 በመገኘት የማዕከሉን የስራ እንቅስቃሴ ተዘዋውረው በመጎብኘት ለማህበሩም የተለያዩ ድጋፎችን አድርገዋል። በጉብኝቱም የማዕከሉን ሥራ አድንቀዋል፡፡

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ድህረ ምረቃ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ዲን የሆኑት ዶ/ር ተከተል አብርሃም በዕለቱ ተገኝተው ከመምህራን፤ ከሰራተኞችና ከተማሪዎች ያሰባሰቡትን ጥሬ ገንዘብ እና የተለያዩ አልባሳት የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ  ተወካይ በተገኙበት ለማህበሩ ስራ አስኪያጅ ለአቶ ስለሽ ጌታቸው አስረክበዋል፡፡

ማህበሩ በ2000 ዓ.ም. ኪዳነ ምህረትና ባታ በተሰኙ እድሮች በ27 አባላት መነሻነት የተቋቋመ ሲሆን ባሁኑ ስዓት 100 ህፃናትን  የማስተማርና የምግብ አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ከሁለት ሺ በላይ ለሚሆኑ እና ዕድሚያቸው ከ5 ዓመት በላይ ሆነው በደማቸው ኤች.አይ.ቪ ያለባቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ቤት ለቤት በመሄድ ድጋፍ እንደሚሰጥ የማዕከሉ ኃላፊ በዕለቱ ገልጸዋል፡፡

 አቶ ስለሽ ጌታቸው አክለውም  ማህበሩ አገር በቀል እንደመሆኑም ከማህበሩ አባላት መዋጮ ባሻገር የተለያዩ የገቢ ማስገኛ ፕሮግራሞችን የሚያካሂድ እንደሆነ ገልጸው ለታደሙትም የማህበሩ አባል በመሆን  የድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል፡፡