የባሕር ዳር ስቴም ማበልፀጊያ ማዕከል ከወላጆች ጋር ተወያየ

16 Jul, 2025

የባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ሳይንስ፣ ቴክኖሎጂ፣ ኢንጂነሪንግ እና ሒሳብ (STEM) ማበልፀጊያ ማዕከል በመጪው ዓመት ለሚጀምረው ፕሮግራም፣ ልጆቻቸውን በማዕከሉ እያስተማሩ ከሚገኙ ወላጆች ጋር በጃንሞስኮቨ አዳራሽ ውይይት አካሂዷል።

የባሕር ዳር ስቴም ማበልፀጊያ ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት ዶ/ር አለሙ ተስፋዬ የስብሰባውን ዋና ዓላማ ሲገልጹ፣ "ከ2018 ዓ.ም ጀምሮ በበጋ የምናስተምረው 'የሳይንስ ሸርድ' የሚባል ፕሮግራም ስላለን፣ ወላጆች የራሳቸውን አስተዋፅዖ ማድረግ አለባቸው። ምክንያቱም የተማሪ ቁጥር መጨመርን ተከትሎ የኬሚካል ግብዓት፣ የመምህራን እና መሰል ወጪዎች በዩኒቨርሲቲ ሊሸፈን ቢችልም፣ ወላጆች አስተዋፅዖ ሊያደርጉ ይገባል የሚል እሳቤ ስላለን ይህንን መረጃ ለማጋራት እና የነሱን ሀሳብ ለመቀበል ነው" ብለዋል።

ዶ/ር አለሙ አክለውም፣ ማዕከሉ ከአምስተኛ ክፍል ወደ ስድስተኛ ክፍል ካለፉ ተማሪዎች ጀምሮ እስከ አስረኛ ክፍል ለደረሱ ተማሪዎች በክረምት መርሃ ግብር ትምህርት ይሰጣል። ተቋሙ ከ2004 ዓ.ም ጀምሮ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን፣ እስካሁን ያሉትን ወጪዎች በሙሉ በመሸፈን መርሃ ግብሩን ሲያካሂድ ቆይቷል። ዩኒቨርሲቲው ወደፊት ራስ ገዝ ለመሆን እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ የራሱን ገንዘብ ማመንጨት ስላለበት፣ ለዚህም የተለያየ ስራዎችን መስራት እንደሚኖርበት ተናግረዋል። "እስካሁን የምንሰጠውን ከወላጅ አገልግሎት ወደ ወላጅ ተሳትፎ በማሻገር፣ በሚቀጥሉት ዓመታት መርሃ ግብሩን በደንብ ለማጠናከር የወላጆች አስተዋፅዖ መምጣት አለበት በሚለው ተስማምተናል፤ ለዚህም ወላጆችን ማወያየት አስፈልጓል" ሲሉ አስረድተዋል።

በዛሬው ውይይት ላይ በክረምት መርሃ ግብር ልጆቻቸውን የሚያስተምሩ ወላጆች በርካታ ጥያቄዎችን ያነሱ ሲሆን፣ ተቋሙ ከዚህ የበለጠ እንዲሰፋ ለማድረግ ወላጆች አቅማቸው የፈቀደውን ድጋፍ ማድረግ እንዳለባቸው በተለያዩ ተሳታፊዎች ተገልጿል።

ማበልፀጊያ ማዕከሉ በ2004 ዓ.ም በሚስተር ማርክ ጌልፋንድ እና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የገንዘብ ድጋፍ ሲቋቋም፣ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ተማሪዎችን ቁጥር ከፍ የማድረግ ዓላማ እንደነበረው ታውቋል።