
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ4,500 በላይ ችግኞችን መተከላቸው ተገለፀ
BDU
16 Jul, 2025
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ4,500 በላይ ችግኞችን መተከላቸው ተገለፀ
ሐምሌ 8/2017 ዓ.ም (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ምርምር እና የማኅበረሰብ አቀፍ ሥራዎች ጎን ለጎን ማህበራትን በማደራጀት የተሳካ የምድረ ግቢ ሥራዎችን ከመስራት ባለፈ በዛሬው ዕለት ከ22 በላይ ዝርያ ያላቸው ከ4,500 በላይ ችግኞችን በዋናው ግቢ የመምህራን መኖሪያ አካባቢ በማሪታም አካዳሚ፣ በሳይንስ ኮሌጅ እና በዋናው ግቢ ሰራተኞች አማካኝነት የተከላ ፕሮግራም ተካሂዷል፡፡
የችግኝ ተከላውን በማስተባበር የተገኙት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምድረ ግቢ ውበትና ጽዳት ዳይሬክተር ዶ/ር አማረ ቢተው እንደገለፁት ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ በምድረ ግቢ ውበት ስራ ምሳሌ የሚሆን ተግባራትን በመስራት የሚጠቀስ ተቋም በመሆኑ የአካባቢውን ስነ ምህዳር ያገናዘበ ፅዳቱንና ውበቱን ለመጠበቅ የሚያስችሉ አገር በቀል ዛፎችን መትከል ኢኮቱሪዝሙን ለመጠበቅ በትኩረት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ አክለውም የግቢውን ውበት በሳር እና በአበባ ከማስዋብ ጎን ለጎን ሀገር በቀል ዛፎችን እና አትክልትና ፍራፍሬዎችን እንዲሁም የቅመማ አቅመም ችግኞችን መትከል ከግቢ ውበት ባለፈ ለምግብነት ጠቀሜታን የሚሰጡ በመሆኑ አበርክቶአቸው የጎላ መሆኑን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል፡፡
በዛሬው ዕለት ከ22 በላይ ዝርያ ያላቸው ከ4,500 በላይ ችግኞችን በዋናው ግቢ እና በመምህራን መኖሪያ አካባቢ የተተከሉት ችግኞች በማህበራት ካሬ ውስጥ በመሆኑ ሰራተኞች ዓመቱን ሙሉ ስለሚንከባከቧቸው ከመድረቅ ስጋት ነፃ መሆናቸውን እና ቀጣይ ለአገልግሎት እንደሚጠበቁ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምድረ ግቢ ውበትና ጽዳት ዳይሬክተር ዶ/ር አማረ ቢተው ተናግረዋል፡፡
በምድረ ግቢ ውበት ዳይሬክተር አማካኝነት ከዓመት በፊት የተተከሉ የተሻሻሉ ዝርያ ያላቸው የሙዝ ችግኞች በሚገባ አድገው ምርት በመስጠት ላይ መሆናቸውን የገለፁት ዳይሬክተሩ በምርት ስብሰባ ላይ እስካሁን ወጥ የሆነ መመሪያ ባለመኖሩ የምርት ብክነት መኖሩን ገልፀው ችግሩን ለመፍታት መመሪያዎችን በማዘጋጀት ለዩኒቨርሲቲው ማኔጅመንት በማቅረብ ውሳኔውን በመጠበቅ ላይ መሆናቸውን እና መመሪያው እንዳለቀ ምርቶችን በሚገባ በመሰብሰብ ለሰራተኛው በቀላል ዋጋ እንዲከፋፈል እንደሚያደርጉ ዶ/ር አማረ ተናግረዋል፡፡



