የኢንስቲትዩቱ የፋሽን ዲዛን ተመራቂ ተማሪዎች የፋሽን ትርኢት አቀረቡ

Selam Campus

11 Nov, 2026

“ የፋሽን ዲዛይን ተመራቂ ተማሪዎች ተደራጅተው ሥራ መጀመር ከቻሉ ማሽን እና የመስሪያ ቦታ እንሰጣለን” ፕ/ር ታምራት ተስፋዬ::

የኢንስቲትዩቱ የፋሽን ዲዛን ተመራቂ ተማሪዎች የፋሽን ትርኢት አቀረቡ፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ‹‹ ባሕር ዳርን የፋሽን ከተማ›› ለማድረግ አልሞ እየሰራ የሚገኘው የፋሽን ትምህርት ቤት፣ በልብሳችን ታሪክ እንናገራለን የሚሉት የ4ኛ ዓመት የመደበኛው (regular) ተመራቂ የፋሽን ዲዛይን ተማሪዎች፣ የ5ኛ ዓመት የማታ(extension) የፋሽን ዲዛይን ተመራቂ ተማሪዎች እንዲሁም በክረምት  የፋሽን ካምፕ ሲሰለጥኑ የነበሩ ሕጻናት 7 የተለያዩ collections የፋሽን ትርኢት በኢንስቲትዩቱ የፋሽን አዳራሽ ለታዳሚዎች አቀረቡ፡፡ 



በዝግጅቱ ላይ የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ እና መካከለኛ አመራሮች፣ መምህራን እና ተማሪዎች፣ ታዋቂ ሞዴሎች፣ የሞዴል ቤተሰቦች፣ ጥሪ የተደረገላቸው ተጋባዥ እንግዶች ታድመዋል፡፡

የኢንስቲትዩቱ የፋሽን ትምህርት ቤት ዲን አቶ ሰሎሞን ፀጋዬ በመክፈቻ ንግግራቸው ዝግጅቱ የ4ኛ ዓመት የፋሽን ዲዛይን ተማሪዎች 3ኛ አመት ላይ ለልምምድ ሲወጡ የሰሯቸውን የተለያዩ የፋሽን አልባሳት ለታዳሚው ለማሳየትና ለማስተዋወቅ ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በዝግጅቱ ከቀረቡት አልባሳት ውስጥ ታዳሚው የሚፈልገውን በተመጣጣኝ ዋጋ መግዛት እንደሚችልም ዲኑ አስታውቀዋል፡፡

የ2026 ሞዴል አሸናፊ የሆነው ዓለም አቀፍ (international) ሞዴል ዘላለም ተድላ በዝግጅቱ ላይ ተገኝቶ የፋሽን ዲዛይነር ተማሪዎች ብቃት ያላቸው መሆኑን በአድናቆት በመግለጽ ወደ ፊት ከኢንስቲትዩቱ ጋር በጋራ እንሰራለን ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የኢንስቲትዩቱ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ፕ/ር ታምራት ተስፋዬ በመዝጊያ ንግግራቸው ተማሪዎቹ ባቀረቡት ሥራ እንደተደሰቱ እና እንደኮሩባቸው በመግለጽ ‹‹የፋሽን ዲዛይን ተመራቂ ተማሪዎች ተደራጅተው ከኢንስቲትዩቱ ውስጥ ሥራ መጀመር ከቻሉ ከ30-40 ማሽን እና የመስሪያ ቦታ እንሰጣለን›› በማለት ቃል ገብተዋል፡፡

ተማሪዎቹ ከትላልቅ የፋሽን ድርጅት ውስጥ ለመቀጠር ከተቋሙ ውስጥ ሥራ ለምደው መውጣት እንዳለባቸው ያሳሰቡት ፕሮፌሰሩ በቀጣይ የሥራ እድል ፈጠራ ስልጠና እንደሚሰጣቸውም ተናግረዋል፡፡ በመጨረሻም ጥሩ ስራ ለሰሩ ለፋሽን ዲዛይን መምህራን እና ተማሪዎች የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡