የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎች የFlagship ፕሮጀክት አሸናፊ የሆነውን ምክረ-ሃሳብ ለውይይት አቀረቡ፡፡

Selam Campus

05 Oct, 2026

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ተመራማሪዎች በዩኒቨርሲቲው የFlagship ፕሮጀክት ጥሪ መሰረት አሸናፊ የሆነውን ምክረ-ሃሳብ ለውይይት አቀረቡ፡፡

መስከረም 21/2019 ዓ.ም (BDU-EiTEX) በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጅ ኢንስቲትዩት እንዲሁም ከተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የተውጣጡ አስራ ሁለት የዩኒቨርሲቲዉ መምህራን እና ተመራማሪዎች የተሳተፉበት በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነው Flagship ፕሮጀክት ንድፈ-ሃሳብ የዩኒቨርሲቲዉ አመራር እና መምህራን በተገኙበት ከቡድኑ በተመረጡ አባላት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በሚገኘዉ ሴኔት አደራሽ ፕሮፖዛላቸውን አቀረቡ፡፡



ፕሮጀክቱ ለወደፊት የተዘጋጁ ተማሪዎችን መገንባት፦ ሂሳዊ አስተሳሰብን፣ ችግር ፈቺነትን እና የዲጂታል ቴክኖሎጂ እውቀትን በአማራ ክልል የመጀመሪያ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ውስጥ ማካተት›› በሚል ርዕስ የቀረበ ሲሆን በ30 የሙከራ ትምህርት ቤቶች ውስጥ የ21ኛው ክፍለ ዘመን ክህሎቶችን — ሂሳዊ አስተሳሰብን፣ ችግር ፈቺነትን እና ዲጂታል ማንበብና መጻፍን — በክፍል ውስጥ ትምህርት አሰጣጥ ላይ ሊለኩ የሚችሉና ሥርዓታዊ መገለጫዎች አድርጎ በመተግበር፣ እንዲሁም በክልል ደረጃ ማስፋፊያ የሚሆን የተረጋገጠ ሞዴል በመፍጠር፣ በአማራ ክልል የሚገኘውን የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ጥራት፣ ፍትሃዊነት እና ጽናት ማሻሻል የሚል ዓላማ የያዘ ነዉ፡፡ 

ለ አራት ዓመታት የሚቆየው ይህ ፕሮጀክት የሚተገበረዉ በሰሜን ጎጃም እና በምዕራብ ጎጃም ዞኖች ሲሆን እነዚህ አካባቢዎች የተመረጡበት ምክንያት ጥናቱን በቅርበት ለመከታተልና የፕሮጀክቱ ዓላማ ሞዴል የሚሆኑ ትምህርት ቤቶችን በመፍጠር ከተጠቀሱት አካባቢዎች ባለፈ ተግባራዊ የሚሆን ተማሪዎችን፣ መምህራንን እና በዘርፉ ያሉ አካላትን የትምህርት ምልከታ እና ስርዓትን የተሻለ ለማድረግ መሆኑን ተመራማሪዎች ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክት ፕሮፖዛሉ ከቀረበ በኋላ ታዳሚዎች ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በተመራማሪዎቹ ለተነሱ ጥያቄዎች በቂ ማብራሪያ ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲዉ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዝዳንት ፕ/ር እንየዉ አድጎ ፕሮጀክቱ ከአሁን በፊት ሲሰሩ ከነበሩት የተለየ እና ወደ ተግባር በመለወጥ የማህበረሰቡን ችግር ሊቀርፍ የሚችል እንደሆነ ገልጸዉ በዚህ ፕሮጀክት ትግበራ ዙሪያ የሚያጋጥሙ ተግዳሮቶችን ለመፍታት አስፈላጊውን እገዛ እንደሚያደርጉ ቃል ገብተዋል፡፡