በባሕር ዳር ከተማ የሚስተዋለውን የኢ-መደበኛ አሰፋፈር
Campus Name
23 Feb, 2026
በባሕር ዳር ከተማ የሚስተዋለውን የኢ-መደበኛ አሰፋፈር ችግር ለመፍታት የሚያስችል የምክክር መድረክ ተካሄደ
በባሕር ዳር ከተማ ጣና ክፍለ ከተማ የሚስተዋሉ የኢ-መደበኛ አሰፋፈር (Informal Settlements) ተግዳሮቶችን ለመለየትና ዘላቂ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ለማስቀመጥ ያለመ የውይይት መድረክ ተካሄደ።
መድረኩ የኦስትሪያ መንግስት ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ባከናወኑት ጥናት ላይ ተመስርቶ የተዘጋጀ ነው።
የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በዩኒቨርሲቲው መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አባል የሆኑት ፕሮፌሰር አማረ ሰውነት ሲሆኑ ይህ ወርክ ሾፕ በጣና ክፍለ ከተማ በሚገኙ ባታ እና ወራሚት ቀበሌዎች ላይ የሚኖሩ ኢ-መደበኛ ሰፈሮች ላይ ትኩረት ያደረገ እንደሆነና በኢ-መደበኛ ሰፈራ ላይ ያለውን ችግር ለይቶ ማውጣት እንዲሁም ለፖሊሲ አውጭዎችና አስተግባሪዎች የሚሆን ግባት መስጠትን ዋና ተልኳቸው መሆኑንና ለዚህ ጥናት /ምርምር/ ስራ አምስት የዩኒቨርስቲው መምህራንና ተመራማሪዎች ተመድበው ጥናቱን እያካሄዱ እንደሆነ ገልጸዋል።
እንደ ጥናቱ ግኝት፣ ላለፉት 20 ዓመታት በከተማዋ ያለው የኢ-መደበኛ አሰፋፈር ከሦስት እጥፍ በላይ መጨመሩን የገለጹት በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርስቲው መምህርና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ ዶ/ር አጸደ ደስታ ናቸው። አከለውም በዚህ ጉዳይ ከዚህ በፊት የተናጥል ውይይት መደረጉንና ያሉ ችግሮችን ለመለየት ብዙ ሂደት እንደሄዱና ይህም ወርክ ሾፕ የዚያ አካል እንደሆነና በዚህ ውይይት የጋራ የመፍትሄ አቅጣጫ ለማምጣት ከማህበረሰቡ፣ ከመንግስት አካላትና መንግስታዊ ካልሆኑ አካላት ጋር በጋራ ለመወያየት እንደሆነ ገልጸዋል።
ጥናቱ በኢ-መደበኛ ሰፈራዎች ውስጥ የሚስተዋሉ ችግሮች መኖራቸው በተለይም የቤቶች ደረጃቸውን አለመጠበቅና ለኑሮ ምቹ አለመሆን፣ የንጹህ መጠጥ ውሃ፣ የመንገድ፣ የጤና እና የትምህርት ተደራሽነት እጅግ አነስተኛ መሆን፣ በነዋሪዎች ላይ የሚስተዋለው የኢኮኖሚ አቅም ማነስና የተረጋጋ የገቢ ምንጭ እጥረት ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑንና ለእነዚህ ችግሮች እንደ ዋና ምክንያት የተጠቀሰው የከተማ አስተዳድሩ የኑሮ ደረጃቸውን የሚመጥን የመኖሪያ ቤት ቦታ አለመስጠቱ መሆኑ በመድረኩ ላይ ተገልጿል ። ይህም ነዋሪዎች ወደ ኢ-መደበኛ አሰፋፈር እንዲያመሩ አስገዳጅ ሁኔታዎችን ፈጥሯል።




