የደቡብ አፍሪካ የሳይንስና ኢንዱስትሪ ምርምር ካውንስል (CSIR) ቡድን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ ጉብኝት አደረጉ

Selam Campus

06 Feb, 2026

የደቡብ አፍሪካ የሳይንስና ኢንዱስትሪ ምርምር ካውንስል (CSIR) ቡድን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ ጉብኝት አደረጉ:

(BDU-EiTEX) ጥር 26/2018ዓ/ም የደቡብአፍሪካ የሳይንስና ኢንዱስትሪ ምርምር ካውንስል (CSIR) ልዑክ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያደረገው የሥራ ጉብኝት በሁለቱ ተቋማት መካከል ያለውን አህጉራዊ ትብብር ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር ሲሆን ጉብኝቱየተጀመረውበባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር መንገሻ አየን እና በልዑካን ቡድኑ መካከል በተደረገ ይፋዊ የውይይት መድረክ ነው፡፡ 

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ ይህንን ጉብኝት እና ግንኙነት "የአፍሪካ መፍትሔ ለአፍሪካ ችግሮች" የሚለውን መርህ በተግባር ለመተርጎም የተወሰደ ትልቅ እርምጃ እንደሚሆን ገልጸዋል።

በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (EiTEX) የኢንፎርሜሽን ስትራቴጅክ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር ዶ/ር መድኃኒት በላቸው  ስለ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና EiTEX ገለፃ አድርገዋል

የCSIR የመረጃና ደህንነት ኃላፊ ዶ/ር ጁባ ሙትስዌኒ በበኩላቸው ተቋማቸው ላለፉት 80 ዓመታት በሳይንስና ቴክኖሎጂ ምርምር የደቡብ አፍሪካን የኢኮኖሚ ተወዳዳሪነት ለማሳደግ ያከናወናቸውን ተግባራት አብራርተዋል። ልዑካንቡድኑ የመሰረተ ልማት ጉብኝቱን የጀመረው በኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (EiTEX) ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር በፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ መሪነት ሲሆን፣ በኢንስቲትዩቱ የሚገኙ የፋሽን አዳራሽ፣ የተማሪዎችን የሥዕልና ቅርጻቅርጽ ውጤቶች እንዲሁም ዘመናዊ የማምረቻ ፋብሪካዎችን ተመልክተዋል። ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ ኢንስቲትዩቱ በዘርፉ የኢትዮጵያ ቀዳሚ የልህቀት ማዕከል መሆኑን በመጥቀስ፣ ከCSIR ጋር የሚደረገው ትብብር በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በፈጠራ፣ Digitalization፣ እንዲሁም ዘላቂነት (Sustainability) ላይ በጋራ ለመስራት አዲስ ምዕራፍ እንደሚከፍት ገልጸዋል። 

በመቀጠልም በባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (BiT) የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን ዘገየ አስጎብኝነት በ "Seifu Maker Space" (BiTEC) ውስጥያሉ የፈጠራ ሥራዎችን ጎብኝተዋል። ማዕከሉ የፈጠራ ሃሳቦችን ወደ ንግድ የሚቀይር ድልድይ በመሆኑ፣ የደቡብ አፍሪካው CSIR ያለውን ሰፊ የቴክኖሎጂ ሽግግር ተሞክሮ ለኢትዮጵያዊያን ስራ ፈጣሪዎች ዓለም አቀፍ ትስስር ለመፍጠር እንደሚረዳ ዶ/ር ሙሉቀን ገልጸዋል።