ኢንስቲትዩቱ 14ኛውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ አካሄደ
Selam Campus
20 May, 2026
ኢንስቲትዩቱ 14ኛውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ አካሄደ።
ግንቦት 8/2018 ዓ.ም(BDU-EiTEX) በባሕርዳር ዩኒቨርሰቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት እና የአፍሪካ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት በጋራ በመተባበር "የጥጥ ፣ ጨርቃ ጨርቅ፣ እና አልባሳት እሴት ትስስር በአፍሪካ " በሚል መሪ ቃል 14ኛውን ዓለም አቀፍ ኮንፈረንስ ከግንቦት 7-8/2018 ዓ.ም ከተለያዩ ሀገራት በመጡ ምሁራንና አምባሳደሮች፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና የኢንስቲትዩቱ ከፍተኛ አመራሮች፣ መምህራን፣ የአስተዳደር ሰራተኞች፣ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የመጡ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅራቢዎች፣ ስራ ፈጣሪዎች፣ ባለድርሻ አካላትና ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በጥበብ አዳራሽ ተካሄደ፡፡
የአፍሪካ ቆዳና የቆዳ ውጤቶች ኢንስቲትዩት ዋና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር አቶ ኒኮላስ ሙድንግዌ በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግራቸው ይህ ጉባኤ በመላው አፍሪካ የጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ዘርፍ ውጤቶችን ለማሳደግ እስተዋጽኦ ይኖረዋል በማለት ገልጸዋል፡፡ አቶ ኒኮላስ አክለውም እነዚህ ኢንዱስትሪዎች የስራ እድል በመፍጠርና ፈጠራን በማስገኘት የአህጉራችን የኢኮኖሚ እድገት የጀርባ አጥንት ናቸው ብለዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ደ/ር መንገሻ አየነ በበኩላቸው የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት የምርምር ባሕልን በማስተዋወቅ ዩኒቨርሲቲው ወደ ፊት ራስ ገዝና የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለመሆን አቅዶ እየሰራው ላለው ተግባር አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣ የትምህርት ዘርፉንና ኢንዱስትሪውን እንደ ድልድይ ሆኖ የሚያገናኝ፣ ስራ ፈጣሪ እንዲሁም የትምህርት የልህቀት ማዕከል ኢንስቲትዩት እንደሆነ በመክፈቻ ንግግራቸው ገልጸዋል፡፡
ኢንስቲትዩቱ የዕውቀት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሁም ከተቋሙ አገር አቀፍና አለም አቀፍ አጋሮች ጋር የግንኙነት መረብ ለመፍጠር የሚያገለግል አለም አቀፍ ኮንፈረንስ መሆኑንም ፕሬዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬ በተመሳሳይ ጉባኤው በጨርቃ ጨርቅ አልባሳትና የቆዳ ዘርፎች የምርምር እና የዕውቀት ስርጭትን ለማበረታታት፣ ለማሳደግና ለማዳረስ ያለመ ነው ብለዋል፡፡


በኮንፈረንሱ ላይ ፓናል ውይይቶች፣ በተለያዩ በሀገር ውስጥ እና በውጭ ሀገራት ሙሁራን ጥናታዊ ጽሑፎች በፊት ለፊት እና በበይነ መረብ ቀርበው ውይይት ተካሂዶባቸዋል፤ የኢንስቲትዩቱ ሌዘር ኢንጅነሪግ ተማሪዎች፣ ከተለያዩ ቦታዎች የመጡ የቀድሞ የኢንስቲትዩቱ ተማሪዎች የነበሩ ስራ ፈጣሪዎች እና አምራች ድርጅቶች ምርቶቻቸውን አስተዋውቀዋል፡፡ በማጠቃለያው ፕሮግራም ላይም ለኮንፈረሱ መሳካት አስተዋጽኦ ላደረጉ ግለሰቦች እና ተቋማት የምስክር ወረቀት ተሰጥቷል፡፡

በመጨረሻም የኢትዮጵያ ሳይንስ እና ስራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ተከተል ዮኃንስ የመዝጊያ ንግግር አድርገው የፋሽን ዲዛይን ተማሪዎች እና ህጻናት የፋሽን ሾው ትርኢት በፈለገ ጊዮን ኢኮ ሪዞርት አቅርበዋል።

