Latest News

እንኳን ደስ አለን!
ከተረፈ ምርቶች የፈጠራ ስራ የሰሩ የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረገውን ውድድር አሸነፉ
*********************************************************
ከሰብል እና ከዓሳ ቆዳ ተረፈ ምርቶች የፈጠራ ስራዎች የሰሩ የዩኒቨርሲቲያችን ተማሪዎች በሀገር አቀፍ ደረጃ ተወዳድረው ላስመዘገቡት ውጤት የሽልማት እና የእውቅና ፕሮግራም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ተቋም ግቢ ጥር 23/2014 ዓ.ም ተካሄዷል፡፡
 
ሀገር በቀል መፍትሄዎችን ከማምጣት አንፃር የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ተቋም የቢዝነስ ኢንኩቤሽን እና ቴክኖ ኢንተርፕርነርሺፕ ሴንተር (BiTec) ተማሪዎች ከዳጉሳ ገለባ፣ ከገብስ ገለባ እና ከሩዝ ገለባ የወረቀት፣ ከአኩሪ አተር ተረፈ ምርት ኮላ /ማጣበቂያ / እንዲሁም ከዓሳ ቆዳ ተረፈ ምርት የመዋቢያ ሎሽን የፈጠራ ስራ ስራዎች በማቅረብ በሀገር አቀፍ የውድድር መድረክ ላይ ተሳትፈው አሸናፊ ሆነዋል፡፡ ለዚህ ስኬት በገንዘብና በማቴሪያል ድጋፍ ላደረጉ ለGiZ እና ሌሎች አጋር ድርጅቶች የሽልማትና የእውቅና አሰጣጥ ስነ-ስርዓት መካሄዱን የተቋሙ ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ ተናግረዋል፡፡
 
የቢዝነስ ኢንኩቤሽን እና ቴክኖ ኢንተርፕረነርሺፕ ሴንተር (BiTec) ዳይሬክተር ዶ/ር አማረ ካሳው ተማሪዎች ያላቸውን የፈጠራ ሃሳብ መሰረት በማድረግ ግምገማ ተደርጎ በስልጠና እንዲዳብር ተደርጎ የናሙና ስራው ከተሰራ በኋላ የስራና ክህሎት ሚኒስቴር በሀገር አቀፍ ደረጃ ወደ ቢዝነስ የሚቀየሩ የፈጠራ ስራዎችን ውድድር ሲያወጣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት አምስት የፈጠራ ስራዎችን አሳትፏል፡፡ በዚህም መሰረት ሦስቱ አሽንፈው ተሸላሚ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ ተማሪዎች እና ሰራተኞች ቴክኖሎጂዎችን በማሳደግ እና በመፍጠር ወደ ቢዝነስ እንዲሸጋገሩ እና የስራ እድል እንዲፈጥሩ በBiTec ስር የኢኖቬሽን ባህልን ለማሳደግ የሚረዳ BiT Maker Space አቋቁሞ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
 
በእውቅና እና በሽልማት አሰጣጥ ስነ-ስርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ ተገኝተው ለተሸላሚዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ እና የማነቀቃቂያ ንግግር አድርገዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን ንግግር (Public Speech) አደረጉ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ሳይንቲፊክ ዳይሬክተር ዶ/ር ሰይፉ አድማሱ ለእንግዶችና ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው የቀድሞ የተቋሙ ምሩቅና በአገሪቱ ብሉም በውጭ አገራት ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረከቱ ምሁራን ለንግግር ወደ ተቋማቸው በመምጣታቸው አመስግነዋል፡፡

ዶ/ር ሰይፉ አክለውም ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመቱን ለማክበር በዝግጅት ላይ መሆኑን አውስተው ይህ ፕሮግራም ለ60ኛ ዓመቱ ዋዜማ ማድመቂያ እንደሚሆንና የቀድሙ ተማሪዎች ስብጥር በርካታ ተግባራትን በማከናወን ጉልህ ፋይዳ እንዳላቸው ተናግረዋል፡፡

መርሃ-ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ተመራቂ ተማሪዎች በተመረቁበት ተቋም እንደሚኮሩ ሁሉ ዩኒቨርሲቲውም እንደነዚህ ታዋቂና አንጋፋ ሙሁራን ማፍራቱ ታላቅ ደስታ እንደሚሰማው ገልፀዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ በማስከተል ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በማንኛውም መስፈርት በአገሪቱ ካሉ ዩኒቨርሲቲዎች ከአዲስ አበባበ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ እንደሚገኝና ከአፍሪካ ደግሞ 100 ምርጥ ዩኒቨርሲቲዎች ዝርዝር ውስጥ መካተቱን አስገንዝበዋል፡፡

በተጨማሪም ዩኒቨርሲቲው አሁን ላይ በበርካታ ግቢዎች ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን በሰፊው አስተዋውቀው የቀድሞ  ተማሪዎች ቡድን መቋቋሙ ለዩኒቨርሲቲውም ሆነ ለከተማው ልማት ፈር ቀዳጅ መሆኑን ፕሮዘዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ አክለውም ዩኒቨርሲቲው የከተማውን ውበት ለማስጠበቅ ማስተር ፕላኑን ሲሰራ የካበተ ልምድ ያላቸውና በዛሬው ዕለት ንግግር የሚያቀርቡት ኢንጅነር ግርማ አላሮ የእንበሳውን ድርሻ መውሰዳቸውን አውስተው 60ኛ ዓመቱን ስናከብር የቀድሞ ምሩቃንን ከማሰባሰብ ጎን ለጎን የነበረውን ለመግለፅ ብቻ ሳይሆን ለወደፊት የትኩረት አቅጣጫም ለመለየት ታልሞ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ከቀረቡት የንግግር ርዕሶች ውስጥ፡-

Ø  ኢንጅነር ግርማ አላሮ በ1962 ዓ.ም የቀድሞ ስሙ ፖሊ ቴክኒክ የተመረቁ ሢሆን "International Building Code and How to Build 21 Century Cities" በተሰኘ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሰፊ ንግግር አቅርበዋል፡፡

Ø ኢንጅነር ግዛቸው ሽፈረው በ1963ዓ.ም በፖሊ ቴክኒክ የተመረቁና "Technology Transfer/ Acquisition for Sustainable Development of Ethiopia" በተሰኘ ርዕሰ ጉዳይ ላይ ያቀረቡ ሲሆን የቴክኖሎጂ ሽግግር ከቃል በዘለለ በአገራችን ላይ ተግባራዊ ያደረገው የኢትዮጲያ አየር መንገድ ነው ብለዋል፡፡

Ø አቶ ብርሃን መዋ በ1963 ዓ.ም ከዚሁ ተቋም የተመረቁ ሲሆን " Education and Knowledge, An Entrepreneur’s Experience" በሚል ርዕሰ ጉዳይ ላይ ሲያቀርቡ ትምህርት እውቀትን የማግኘት ሂደት ሲሆን የተማረ ሁሉ ያውቃል፣ ያልተማረ ሁሉ አያውቅም ማለት እንዳልሆነ በሰፊው አውስተዋል፡፡

መድረኩን የመሩት በተመሳሳይ  ግዚያት የተመረቁና ታዋቂው ኢንጅነር ሸዋአፈራው ግርማ ናቸው፡፡

በመጨረሻም የዩኒቨርሲቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጅክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ ላቅራቢዎች ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበው ዩኒቨርሲቲውን የሚያስተዋውቅ ስጦታ ለአራቱም እንግዶች አበርክተዋል፡፡

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

 

በትህነግ ወራሪ ቡድን የደረሰውን ጉዳት መረጃ የሚሰበስበው ግብረ ሃይል ስራውን አጠናቀቀ

በክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ ዋና ባለቤትነት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና በአማራ ክልል ከሚገኙ ሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመቀናጀት በትግራይ ወራሪ ቡድን የደረሰውን ቁሳዊ፣ ስነልቦናዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳት መረጃ በመሰብሰብ የሚመለከተዉ አካል ተመጣጣኝ የሆነ ድጋፍ ለማድረግ በሚያስችል መልክ አጥንቶ በመሰነድ የመልሶ ማልማት ስልታዊ ዕቅድ ለማዘጋጀት ዓላማን አንግቦ ሲሰራ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተቋቋመው ግብረሃይል በሁለት ቡድን የተከፈለ ሲሆን ቡድን አንድ በዶ/ር አቸነፍ ሞትባይኖር አስተባባሪነት በመቄት ወረዳ ቡድን ሁለት ደግሞ በአቶ ደመቀ ላቀው አስተባባሪነት በጋዞ እና አንጎት ወረዳዎች እንዲሁም በጋሸና ከተማ መስተዳድር የቤተሰባዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ተቋማት ላይ መረጃዎችን ሰብሰቦ በማጠናቀቅ ለክልሉ ፕላን እና ልማት ቢሮ ተወካይ አስረክቧል፡፡

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲው ተገኝተው "ህዝባዊ ዲስኩር እያቀረቡ ነው

በባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ተቋም ትምህርታቸውን በ1960ዎቹ አጠናቀው በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች በስራ ላይ የሚገኙ ስኬታማ የቀድሞ የዩኒቨርስቲው ተማሪዎች እውቀትን በተቋደሱበት ተቋም በመገኘት ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ህዝባዊ ዲስኩር በማቅረብ ላይ ናቸው።

የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዚደንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘን ጨምሮ ከፍተኛ አመራሮች እና መምህራን መድረኩን በመታደም ላይ ናቸው።

በአምባሳደር ኢንጂኔር ዶ/ር ስለሽ በቀለ የተመራ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስራ አመራር ቦርድ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታልን ጎበኘ።

ሙሉ ዘገባውን ለማግኘት ፡-https://www.facebook.com/cmhsbdu/posts/1931836510351258

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋም ዘመናዊ ቤተ መጽሐፍት ተመረቀ።

 

በባሕር ዳር   ዩኒቨርሲቲ  የኢትዮጵያ  ቴክስታይልና  ፋሽን ቴክኖሎጂ ተቋም ያስገነባውን በርካታ አገልግሎቶችን መሰጠት የሚችል የቤተ መጽሐፍት ሕንጻ አስመርቋል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ  የኢትዮጵያ  ቴክስታይልና  ፋሽን  ቴክኖሎጂ  ተቋም  ሳይንቲፊክ  ዳይሬክተር ዶ/ር ታምራት ተስፋዬ በመክፈቻ ንግግራቸው ዩኒቨርስቲው በ1956 ዓ.ም ፖሊ ቴክኒክ በሚል ስያሜ ተመስርቶ አገልግሎት መስጠት ከጀመረበት ጀምሮ በመማር ማስተማር፣ በምርምርና በማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን በመስራት ለሀገር እድገት የሚጠበቅበትን እየሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ዛሬ የምናስመርቀው ቤተ መጽሐፍት የማህበረሰብ ቤተ-መጽሐፍት (Community Library፣  የህጻናት ቤተ-መጽሐፍት፣ ሰፊ ቦታ ያለው ሰገነት፣ አረንጓዴ ቤተ-መጽሐፍት (Green Garden Library)፣ የድህረ ምረቃ እና ሴቶች  ቤተ መጽሐፍት፣  የምርምር ክፍል፣ የቡድን  ጥናት  ክፍል፣ የሰገነት ማንበቢያ፣ ቢሮዎች፣ ምግብ ቤትና ካፍቴሪያዎች ማሟላቱን ጠቁመዋል፡፡ ቤተ መፅሀፍቱ የአካባቢውን  ማህበረሰብ ተጠቃሚ ለማድረግአገልግሎት እንደሚሰጥ ገልጸዋል፡፡

 

ባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ፐሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በስነ-ስርአቱ ላይ በመገኘት እንደተናገሩት ዩኒቨርሲቲው የመጀመሪያ ትውልድ ዩነቨርሲቲ ይሁን እንጂ የመሰረቱት ፖሊ እና ፔዳ የሚያስፈልጋቸውን ሳያሟሉ ለአመታት እንደቆዩ አውስተዋል፡፡ ዛሬ ላይ ግን በልዩ ትኩረት ሲሰራበት የቆየው ቤተ መጽሐፍት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ  አመራር  ቦርድ  ሰብሳቢ  አምባሳደር ኢንጅነር ስለሺ በቀለ በተገኙበት መመረቁን እንዲሁም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 60ኛ ዓመት የወርቅ እዮቤልዩ በድምቀት ለማክበር የተለያዩ ኮሚቲዎች ተቋቁመው በርካታ ስራዎች 

እየተከናወነ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመዋል።

 

የእለቱ የክብር እንግዳ ክቡር አምባሳደር ኢንጂነር ዶ/ር ስለሽ በቀለ በበኩላቸው መምህራን በክፈል ውስጥ ሰፊ ገለፃ በማድረግ እውቀት ቢያስተላልፉም፤ ስራቸው ውጤታማ እንዲሆን ተማሪዎች ዕውቀታቸውን የበለጠ ለማጎልበት እንደዚህ ያሉ ቤተ መፅሐፍት ያስፈልጉናል ሲሉ ገልፀዋል፡፡ አሁን ላይ እየገጠመን ያለውን የለብ ለብ ንባብ ሶሻል ሚዲያ እና ኢንተርኔት ጥገኛ የመሆን አዝማሚያ እና ከንባበ የራቀውን ወጣት ወደ ንባብ እንዲመለስ ለማድረግ ቤተ መጽሐፍት የጎላ አስተዋፆ አላቸው ብለዋል፡፡  

በምረቃ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ ሰብሳቢ አምባሳደር ዶ/ር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ ፣ የዩኒቨርሲቲ አመራሮች  እና ሌሎች ጥሪ  የተደረገላቸው  እንግዶች  ተገኝተዋል።

በመጨረሻም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሥራ አመራር ቦርድ አባላት እና የዩኒቨርሲቲ አመራሮች የሕክምና እና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ /ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ያሰገነባቸውን ኦክስጅን ማምረቻ፣ ዘመናዊ የደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ፣ የተጣራ ውሃ ማምረቻ እንዲሁም በቅርቡ የሚጀምሩ የህክምና መሳሪያዎችን ጎብኝተዋል፡፡ 

 

 

 

የብቁ አመራር ማበልፀጊያ መድረክ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ሕክምናና ጤና ሣይንስ ኮሌጅ የአመራሮችን ክህሎት ለማዳበርና የተከናወኑ ተግባራትን ብሎም የወደፊት የትኩረት አቅጣጫን መለየት ላይ ትኩረት ያደረገ ለሁለት ተከታታይ ቀናት የሚቆይ ውይይት በጥበብ ህንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በመካሄድ ላይ ነው፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ፕሮግራሙን ላዘጋጀው አካል ምስጋና አቅርበው የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፍኖተ ካርታና ቁልፍ መልዕክት በተሰኘ ርዕሰ-ጉዳይ ላይ ሰፊ ማብራሪያ አቅርበዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በአገሪቱ ካሉት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ አንጋፋ ተቋም መሆኑን ሲያወሱ 409 መርሃ ግብሮች በመዘርጋት፣ በተለያዩ ኮሌጆች፣ፋኩልቲዎች፣ኢንስቲትዮቶችና አካዳሚዎች አማካኝነት በ9 ግቢዎች በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን ፕሬዘዳንቱ ካቀረቡት ፅሁፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡

የኮሌጁ ዋና ስራ አስፈፃሚ ፕ/ሮ የሽጌታ ገላው ጥሪውን አክብረው ለመጡ ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው የኮሌጁን የ 10 ዓመት ስትራቴጅ እቅድና በ2011-2013 በጀት ዓመት የተከናወኑትን አበይት ተግባራት እንዲሁም ተቋማዊ የሶስት ዓመት ጉዞና ዕድገት በዝርዝር አቅርበዋል፡፡

ኮሌጁ በስፋት ከባሕር ዳር ኢንስቲትዩት ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ የሚገኝ እነደሆነና በበጀት አጠቃቀም ግን የዩኒቨርሲቲውን በጀት 1/3 በመጠቀም አንደኛ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ ካቀረቡት ፅሁፍ ለመረዳት እንደተቻለው ኮሌጁ ከዛሬ 13 ዓመታት በፊት በዶ/ር ፀሐይ ጀንበሩ መሪነት በአንድ መምህር የተቋቋመ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከ600 በላይ መምህራን ከ1000 በላይ የአስተዳደር ሰራተኛ ያለው ጠንካራ ተቋም ነው፡፡

ኮሌጁ 9 አባላት ያሉት ቦርድ ያቋቋመና ተጨማሪ 8 የልህቀት ማዕከል ለማቋቋም ከከተማ አስተዳደሩ ለማስፋፊያ 138 ሄክታር መሬት ጠይቆ ሳይውል ሳያድር 108 ሄክታር መሬት መረከቡን ከፕሮፌሰሩ ሪፖርት ለመረዳት ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ሌሉች ሪፖርቶችና ፅሁፎች በመቅረብ ላይ ይገኛሉ፡፡

በሙሉጉጃም አንዱዓለም

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዘንዘልማ ግቢ የህጻናት ማቆያ ማዕከል ተመርቆ ስራ ጀመረ

*******************************************************************************

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የግብርናና አካባቢ ሳይንስ ኮሌጅ ለሴት የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን እፎይታ የሚሰጥ የህጻናት ማቆያ ለመጀመሪያ ጊዜ ስራ ሲጀምር በዩኒቨርሲቲው ውስጥ ተቀጥረው በማገልገል ላይ የሚገኙ 67 ህጻናትን መቀበሉ በምረቃው ላይ ተገልጿል፡፡

የፕሮግራሙን መጀመር ያበሰሩት የኮሌጁ የስነ-ምድር ት/ቤት ዳይሬክተር ዶ/ር ምንያህል ተፈሪ ለሴት የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህራን በፆታቸው ምክኒያት ከስራ ገበታቸው ወደኋላ እንዳይቀሩና ሙሉ አቅማቸውን ተጠቅመው ውጤታማ ስራ እንዲያስመዘግቡ የህፃናት ማቆያው መከፈት ጉልህ አስተዋጾ እንደሚኖረው ተናግረዋል፡፡

የማቆያ ማዕከሉን ለማስጀመር በርካታ ውጣ ውረዶች እንደነበሩ ገልፀው ለመወያያ የመነሻ ፅሁፍ ያቀረቡት የኮሌጁ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ታደሰ መኳንንት በዩኒቨርሲቲው ካሉት ግቢዎች መካከል በሶስቱ ግቢዎች ማለትም በፔዳ፣ፖሊና ሰላም ካምፓሶች የህፃናት ማቆያ የተከፈተ ቢሆንም በመልማት ላይ ካሉት ግቢዎች መካከል የዘንዘልማ ግቢ የመጀመሪያው ግቢ ሊባል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡

የፆታ እኩልነትን እውን ለማድረግና የእናቶችን የስራ ጫና ለመቀነስ ታልሞ ማዕከሉ እንደተከፈተ እና በአሁኑ ወቅትም 6 ሞግዚቶችና 2 የፅዳት ሰራተኞች በድምሩ 8 ሰራተኞችን በመቅጠር የ67 እናቶችን ህፃናት በመቀበል ስራ መጀመሩን ከቀረበው ፅሁፍ ለመረዳት ተችሏል፡፡

በፕሮግራሙ ላይ ማእከሉ እንዲከፈት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱት የኮሌጁ የሴቶች፣ህፃናትና ወጣቶች ባለሙያ ወ/ሮ ገነት ከበደ የምስክር ወረቀት ተበርክቶላቸዋል፡፡

ለሴቶች ምቹ የስራ ሁኔታ ፈጥሮ ሙሉ አቅማቸውን መጠቀምና ወደ አመራር እንዲመጡ ማብቃት ለሴቷ ብቻ ሳይሆን ለተቋሙ ብሎም ለሀገር እድገት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑን የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር ጉዳዩች ም/ፕሬዚዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ የመርኃ-ግብሩን ማጠቃለያ ንግግር ሲያደርጉ ከአሁን በፊት በነበሩት አመራሮች ማቆያው ሊከፈት ታስቦ እንደነበረና በተለያዩ ምክንያቶች መዘግየቱን አውስተው አሁን ላይ ስራ መጀመሩ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ ገድፍ አክለውም ከሰራተኛው የተነሱት አንዳንድ ጥያቄዎች በሂደት እየታዩ መልስ የሚያገኙ እንደሆኑና ዩኒቨርሲቲው ክትትልና ድጋፉን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ተናረዋል፡፡ አክለውም  ይህ አይነት  ምቹ የስራ ሁኔታ ሲፈጠር ሁሉም ሰራተኛ በስራ ሰዓት የስራ ገበታው ላይ በመገኘት የተሰጠውን ተግባር በብቃት መወጣት እና የበኩሉን አስተዋጽኦ ማበርከት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

 

የኢትዮጵያ ቴክስታይል እና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩትን ላለፉት ዓመታት በሳይንቲፊክ ዳይሬክተርነት ሲያገለግሉ ለቆዩት ዶ/ር አበራ ከጪ የምስጋና እና የዕውቅና ፕሮግራም ተካሄደ፡፡

የዜናውን ሙሉ ለማግኘት፡- https://www.facebook.com/eitex.et/posts/354747073317151

የስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል የመጀመሪያ ሁለት የዶክትሬት ዲግሪ ተማሪዎች የመመረቂያ የጥናት ውጤታቸውን ተቋቁሞ በስኬት አጠናቀቁ

     *********************************************************************************

(ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ ጥር 14/2014ዓ/ም)

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል ሁለት የዶክትሬት ተማሪዎች ፔዳ ግቢ በሚገኘ ኦዲቴሪየም አዳራሽ የመመረቂያ የጥናት ውጤታቸውን ተቋቁሞ በማድረግ የሦስተኛ ዲግሪያቸውን ውጤታማ በሆነ መንገድ በማጠናቀቅ በትምህርት ክፍሉ ታሪክ የመጀመሪያ ሆነዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ  የሦስተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን ጥናትና ምርምር ግምገማ ፕሮግራም አስመልክተው  ዩኒቨርሲቲው ያስቀመጠውን ራዕይና ግብ ለማሳካት እየተሰሩ ካሉ ተግባራት መካከል በስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል መሬት ላይ ያለው የፕሮግራም ስብጥርና በምርምር ህትመት ውጤቶች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2000 ዓ.ም የስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል ከፍቶ የመጀመሪያ ዲግሪ ፕሮግራም ማስተማር እንደጀመረ፤ በ2007 ዓ.ም የማስተርስ ፕሮግራም እንዲሁም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በዶክትሬት ዲግሪ ፕሮግራም እያስተማረ እንደሚገኝ ዶ/ር እሰይ ከበደ አውስተዋል፡፡

ዩኒቨርሲቲው በ2025 መሪ የስታቲስቲክስ ትምህርት ክፍል የማድረግ ራዕይና ተልእኮን አንግቦ በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ በዚህም በስታቲስቲክስ ዘርፍ ከ20 በላይ የተለያዩ የህትመት ውጤቶች ታትመው አገልግሎት ላይ መዋላቸው ተገልጿል፡፡

የስታስቲክስ ትምህርት ክፍል ኃላፊ ዶ/ር ደነቀው ቢተው በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው እንደገለፁት ትምህርት ክፍሉ የዳታ ሳይንስ ትምህርት ካሪኩለም አዘጋጅቶ የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎችን በ2015ዓ.ም ተቀብሎ ለማስተማር እየሰራ ይገኛል፤ ይህም በኢትዮጵያ የመጀመሪያው መርሀ ግብር ያደርገዋል ብለዋል ፡፡

የድህረ-ምረቃ ፕሮግራሞችን በማስፋት የምርምር ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ሲሆን ፤ ለዚህም የዛሬዎቹ ተመራቂዎች ለትምህርት ክፍሉ ትልቅ ጉልበት ይሆናሉ ተብሏል፡፡

በእለቱ አንዱ የሆነው የሦስተኛ ዲግሪ የመመረቂያ ጥናት ፅሁፍ አቅራቢ እጩ ዶ/ር ኃይሌ መኮንን በህጻናት የአመጋገብ ስርአት ላይ ወቅቱን የሚመጥን የስታስቲክስ መተንተኛ ስልት መጠቀም ላይ ያተኮረ ጥናት ማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡ አቅራቢው ከአሁን በፊት ሰባት ደረጃቸውን የጠበቁ የጥናት ስራዎች የሰሩ ሲሆን ከእነዚህ የጥናትና ምርምር ስራዎች ውስጥ አራቱ በታወቁ አሳታሚ ድርጅቶች ታትመዋል፡፡ በጥናቱ በኢትዮጵያ የሚገኙ 72 ዞኖች ዳታ ተወስዶ በህፃናት ስርአተ ምግብ መለኪያ መሰረት በማድረግ የሰፋ ችግር ያለባቸውንና የተሻለ የአመጋገብ ስርአት ያለባቸውን ዞኖች ማመላከት የተቻለ መሆኑን ተመራቂው ገልጸዋል፡፡

አቅራቢው የPhD ትምህርታቸውን ለመጨረስ ሦስት አመት እንደወሰደባቸው የገለጹ ሲሆን ሀገሪቱ የገጠማት የህልውና  ችግር የፈጠረውን የስነ-ልቦና ጫና ተቋቁመው  ለመጨረስ በመብቃታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡

ሌላኛው የእለቱ የሦስተኛ ዲግሪ መመረቂያ ፅሁፍ አቅራቢ ሰናሀራ ኮርሳ (Senahara korsa) ሲሆን Analysis of Longitudinal Child Growth Trajectories በሚል ርእስ ጥናት ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የስታስቲክስ ትምህርት ክፍል በ2014 ዓ.ም 14 የዶክትሬት ተማሪዎችን በተለያዩ ፕሮግራሞች እያስተማረ ይገኛል፡፡

ዘጋቢ፡- አለባቸው አለሙ

Pages