
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና አፍሪካን ሬነሰንስ ቴሌቪዥን (Arts TV) ስትራቴጂያዊ የሚዲያ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
08 Oct, 2025
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና አፍሪካን ሬነሰንስ ቴሌቪዥን (Arts TV) ስትራቴጂያዊ የሚዲያ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ፣ መስከረም 28/ 2018 ዓ.ም. -- ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከአፍሪካን ሬነሰንስ ቴሌቪዥን (Arts TV) ጋር በትምህርት፣ ምርምር፣ ሥራ ፈጠራና ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ዙሪያ በትኩረት ለመሥራት የሚያስችል ስትራቴጂያዊ የሚዲያ አጋርነት ስምምነት በይፋ ተፈራረመ። ይህ ስምምነት ሁለቱ ተቋማት የጋራ ራዕያቸውንና ዕቅዶቻቸውን በብቃት ለኅብረተሰቡ ለማድረስ ያላቸውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።
የአጋርነቱ ዋነኛ ዓላማ የዩኒቨርሲቲውን ትምህርታዊና ምርምራዊ ሥራዎች፣ የሥራ ፈጠራ ተነሳሽነቶችን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን ለሕዝብ ተደራሽ ማድረግ ነው።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ግንኙነት እና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ግርማው አሸብር፣ ዩኒቨርሲቲው ከአርትስ ቴሌቪዥን ጋር ለረጅም ጊዜ 'ፈትል' የተሰኘ የቴሌቪዥን ፕሮግራምን ጨምሮ በርካታ ሥራዎችን በጋራ ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል። አክለውም፣ ዩኒቨርሲቲው በቀጣይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለሕዝብ ለማድረስ፣ አዲሱን ርዕይ 'ጥበብ ቁጥር 2' የተሰኘውን የአምስት ዓመት የራስ ገዝ የሽግግር እቅድ በሚገባ ለመፈጸም እና ለተለያዩ የሥራ ዕቅዶች ስልታዊ የሚዲያ አጋር ለመሆን አርትስ ቴሌቪዥን "ተቀዳሚ ምርጫ" መሆኑን ገልጸዋል።
የአፍሪካን ሬነሰንስ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ዳንኤል በላይነህ በበኩላቸው፣ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር መሥራት "የሚያኮራ ተግባር" መሆኑን ገልጸው፣ ስምምነቱ አፍሪካን በእውቀት ለማስተሳሰር ትልቅ ሚና እንደሚጫወት አመላክተዋል። በተጨማሪም፣ Arts TV ከዛሬ ጀምሮ "የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚዲያ ወኪል" ሆኖ እንደሚያገለግል ተናግረዋል። አቶ ዳንኤል በላይነህ በተለይም እንደ ስነሆሳዕና ማዕከል፣ የአባይ የባሕልና የቋንቋ ጥናት ተቋም፣ የዋሸራ ዲኦስፔስና ራዳር ሳይንስ ማዕከል ያሉ የአገር በቀል ዕውቀት ማዕከላት መኖራቸው ለአገር ዕውቀት መዘመን ተስፋ የሚሰጥ መሆኑን አድንቀዋል።
በስምምነቱ ፊርማ ሥነ-ሥርዓት ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንትን ወክለው የተገኙት የህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር በቃሉ ውብሸት በሰጡት አስተያየት፣ የአርትስ ቴሌቪዥን የመመሥረቻ ግብ ከዩኒቨርሲቲው ዓላማ ጋር የሚመሳሰል መሆኑን ገልጸዋል። ሁለቱም ተቋማት አፍሪካን በትምህርት እና በሚዲያ ዘርፍ ተደራሽ ለማድረግ መነሳታቸው ስምምነቱ ስኬታማ እንዲሆን ዋነኛው መሠረት መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል። ዩኒቨርሲቲው ለጥበብ ቅድሚያ መስጠቱ፣ በአፍሪካ ምርምር ተኮር ከሆኑ ቀዳሚ ዩኒቨርሲቲዎች አንዱ ለመሆን መትጋቱ እና አህጉራዊ ራዕይ መሰነቃቸው ተቋማቱን የሚያመሳስላቸው እንደሆነም ገልጸዋል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በርካታ ምሁራንን ያፈራ አንጋፋ የምርምር ተቋም ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት በዘጠኝ ካምፓሶች ከ30 ሺህ በላይ ተማሪዎችን እያስተማረ ይገኛል።
