
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ "ሠላም አካዳሚ" የማህበረሰብ ትምህርት ቤት በይፋ አስጀመረ
01 Oct, 2025
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ "ሠላም አካዳሚ" የማህበረሰብ ትምህርት ቤት በይፋ አስጀመረ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ - (መስከረም 20 ቀን 2018ዓ/ም)የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት አካል የሆነው "ሠላም አካዳሚ" የተሰኘው የማህበረሰብ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን ተቀብሎ ሥራ መጀመሩን አስታወቀ። አካዳሚው የዩኒቨርሲቲውን ሠራተኞች ለመደገፍና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ ያለመ ነው።
ከዚህ ቀደም በ2017 ዓ.ም. የቅድመ መደበኛ (KG 1 እስከ KG 3) ትምህርትን ሲሰጥ የቆየው ሠላም አካዳሚ፣ በዚህ ዓመት ደግሞ ከ1ኛ እስከ 6ኛ ክፍል ያሉ ተማሪዎችን በመቀበል ሙሉ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት መስጠት ጀምሯል። ይህ መስፋፋት የዩኒቨርሲቲው ለሠራተኞቹ ከሚሰጣቸው የማህበረሰብ አገልግሎቶች መካከል ዋነኛው ሲሆን፣ በተለይም የሠራተኞችን ከኑሮ ውድነት አንጻር ያለውን ጫና በማቅለል ረገድ ትልቅ ድጋፍ እንደሚሰጥ ይጠበቃል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ለትምህርት ቤቱ መቋቋም የቅርብ ክትትል በማድረግ በሰው ሃይልና በግብዓት ተሟልቶ በሙሉ አቅም ስራ እንዲጀምር አድርገዋል። ፕሮፌሰር ታምራት ተስፋዬን ጨምሮ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (EiTEX- BDU) ሰራተኞች አካዳሚው እንዲቋቋም ከፍተኛ ድርሻ ተወጥተዋል። ትምህርት ቤቱን ስራ ለማስጀመር ከሠራተኞችና ከተማሪ ወላጆች ጋር የውይይት መድረክ የተደረገ ሲሆን፣ የትምህርት ጥራት መላሸቅና የግል ትምህርት ቤቶች የዋጋ መናር ባለበት ወቅት ትምህርት ቤቱ መከፈቱ ትልቅ ደስታ እንደፈጠረላቸው ወላጆች ገልጸዋል። በውይይቱ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከ60ዓመታት በላይ ያለምንም ሞዴልና ማህበረሰብ ትምህርት ቤት የቆየ በመሆኑ አሁን በቁጭት መስራት እንደሚያስፈልግና የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ ተባባሪ እንዲሆንም ጥሪ ቀርቧል።
የሠላም አካዳሚ መማር ማስተማር ሂደት ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ሁሉም አስፈላጊ ቁሳቁሶች ሙሉ በሙሉ ተሟልተውለት እንደተጀመረ ተገልጿል። አካዳሚው በቀጣይ ብቁ የሀገር ተተኪዎችን በመቅረጽ የጎላ ሚና እንዲጫወት ታስቦ ትኩረት ተሰጥቶት ለወደፊቱ ሞዴል ትምህርት ቤት ለመሆን ያለመ ነው።
ትምህርት ቤቱ የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በባለቤትነት በመስራት ከፍተኛ አስተዋፅዖ አድርጓል፤ በአሁኑ ጊዜም በዩኒቨርሲቲው ዋና የትኩረት መስክ ሆኖ እየተሰራ ይገኛል።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከዚህ ቀደም የስቲም (STEM) ማዕከል በማቋቋም በቴክኖሎጂ ትምህርት ዙሪያ ሲሰራ መቆየቱ የሚታወስ ሲሆን፣ የሠላም አካዳሚ መጀመርም ጥራት ያለው ትምህርትን ከመጀመሪያ ደረጃ ጀምሮ በማስተማር ልዩ ትምህርት ቤት ለመፍጠር ያለውን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነው።


