የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ ከፍተኛ የሥራ ጉብኝት አካሄደ
19 Nov, 2025
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ (ሕዳር 09/2018ዓ/ም)፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሥራ አመራር ቦርድ በቦርዱ ሰብሳቢ ክቡር አቶ አደም ፋራህ የተመራ ከፍተኛ የሥራ ጉብኝት አካሂዷል። ጉብኝቱ የዩኒቨርሲቲውን ወቅታዊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎች፣ የትምህርት ግብዓቶች፣ የቴክኖሎጂ ማዕከላትን እና የተማሪዎችን የፈጠራ ሥራዎች በቅርበት ለመመልከት ያለመ ነበር።
የሥራ አመራር ቦርዱ ጉብኝቱን የጀመረው በኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (BDU-EiTEX) ሲሆን፣ በውስጥ ለውስጥ የአስፓልት መንገድ ግንባታ፣ በአዳዲስ የማስተማሪያና የአስተዳደር ህንጻዎች ግንባታዎች እንዲሁም ቤተ-ሙከራዎችና የማስተማሪያ ፋብሪካዎች ላይ የተደረገውን ልማት አድንቋል። በተጨማሪም በአፓራል ፋኩልቲና በሥዕልና ቅርጻቅርጽ ተማሪዎች የተዘጋጁትን የፋሽንና የሥዕል አውደ-ርዕይ ተመልክቷል።
በፔዳ ግቢ ደግሞ በአዲስ እየተገነባ የሚገኘውን ግዙፉን የመረጃ ማዕከል (Data Center) የግንባታ ደረጃ የተጎበኘ ሲሆን በባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (BDU-BiT) የተጀመሩትን የመሠረተ ልማት ግንባታዎች ሂደት፣ የቴክኖሎጂ ቢዝነስ ማበልጸጊያ ማዕከሉን (Seifu Maker Space ) እና ከተማሪዎች የፈጠራ ስራ ወደ ቢዝነስ የተቀየሩ ውጤቶችን የምልከታው አካል ነበሩ።
ይህ የሥራ ጉብኝት የተካሄደው የቦርድ አባላቱ ለዩኒቨርሲቲው የቦርድ ስብሰባ በባሕር ዳር ከተገኙበት ጊዜ ጋር ተቀናጅቶ ነው። ጉብኝቱ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት በዶ/ር መንገሻ አየነ አማካኝነት ምልከታና የገለጻ ቅኝት የተደረገበት ነው።
የዩኒቨርሲቲው ስራ አመራር ቦርድ የዩኒቨርሲቲውን ዕድገት ለመደገፍና ለመምራት ያለውን ቁርጠኝነት በጉብኝቱ ያረጋገጠ ሲሆን ለወደፊትም ተመሳሳይ የስራ ጉብኝቶች እንደሚካሄዱ ተነግሯል።


