
በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የሳይንስ ባለሙያዎች ማሕበር ዓመታዊ ዓለማቀፍ አውደ-ጥናት ማካሄድ ጀመረ
11 Aug, 2025
በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የሳይንስ ባለሙያዎች ማሕበር ዓመታዊ ዓለማቀፍ አውደ-ጥናት ማካሄድ ጀመረ
****************************************************
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የሳይንስ ባለሙያዎች ማሕበር ከነሐሴ 05-09/ 2017 ዓ.ም ድረስ ለተከታታይ አምስት ቀናት በምርምር፣ መማር ማስተማር እና በስርዓተ ትምህርት ዙሪያ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ስምንት የዩኒቨርሲቲዎች ጋር በበይነ-መረብ የሚያርገውን ዓለማቀፍ አውደ-ጥናት ማካሄድ ጀመረ፡፡
በዘንድሮው Virtual Summer School የZoom አውደ-ጥናት ላይ የተሳተፉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳይንስ ኮሌጅ ዲን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አሳዬ ማሕበሩ ከተመሰረተበት ከ2000 ዓ.ም ጀምሮ በሳይንስ ትምህርት ዙሪያ እውቀቶችን የመጋራት የመደገፍ፣ የማጎልበትን እና የመማር ማስተማር ሂደቶችን በማሳለጥ፣ የተማሪዎችን የምርምር ስራዎችን በመገምገም፣ በገንዘብ በመደገፍ እንዲሁም የውጭ የትምህርት እድሎችን እንዲያገኙ በማደረግ በርካታ ስራዎችን እየሰራ ያለ ጠንካራ የባለሙያዎች ማሕበር መሆኑን ተናግዋል፡፡ ማሕበሩ ቀጣይ በሳይንስ ፣ በቴክኖሎጂ፣ በምህንድስና እና በሒሳብ መስኮች ላይ የተሻለ አደረጃጀት እና አሰራር ያመጣሉ ብለው እንደሚጠብቁ ፕሮፌሰር ብርሀኑ ተናግረዋል፡፡
የአውደ-ጥናቱ አስተባባሪ የሆኑት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የፊዚክስ ትምህርት ክፍል ኃለፊ ዶ/ር ታምሩ ንጉሴ ስለማህበሩ በሰጡን ማብራሪያ Ethiopian Physics Society in North America ተብሎ ይጠራ የነበው የበለሙያዎች ማሕበር አሁን ላይ ስሙን በሰሜን አሜሪካ የኢትዮጵያ የሳይንስ ባለሙያዎች ማሕበር በሚል ስያሜውን በመለወጥ እና አድማሱን በማስፋት ከፊዚክስ በተጨማሪ የሳይንስ ፣ቴክኖሎጂ፣ምህንድስናን እና የሒሳብ ሙያዎችን በማካተት በትምህርት ዘርፉ በርካታ ስራዎችን እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ የባለሙያዎች ማህበር ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ወጣት ተማሪዎችን በሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ላይ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት ከማሳደግ ጋር ተያይዞ በውጭ ያሉ ዩኒቨርሲቲዎች ጋር ግንኙነቶችን በመፍጠር የተሻለ የትምህርት ዕድል እንዲያገኙ እና ዓለማቀፍ ፈተናዎችን እንዲፈተኑና የተሸለ ውጤት እንዲያስመዘግቡ ስልጠናዎችን ይሰጣል፣ የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል እንዲሁም የውጭ ሀገር የትምህርት እድሎችን ያመቻቻል ሲሉ ዶ/ር ታምሩ ንጉሴ ተናግረዋል፡፡ ኃለፊው አክለውም ማህበሩ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከመጀመሪያ አስከ ሦስተኛ ድግሪ የሚማሩ ተማሪዎችን ውጤታቸውን መሰረት ባደረገ መልኩ የማበረታቻ ሽልማቶችን በየጊዜው እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
የዘንድሮውን ዓመት Virtual Summer School አውደ-ጥናት ለማዘጋጀት ማሕበሩ የሚጠይቀውን ቁሳቁስ በማዘጋጀት እና የገንዘብ ድጋፍ በማድረግ፣ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየን እና የኮሌጁ ዲን ፕሮፌሰር ብርሃኑ አሳዬ ለዝግጅቱ መሳካት ላበረከቱት ጉልህ ሚና ኃለፊው በማህበሩ ስም አመስግነዋል፡፡ የባለሙያዎች ማህበር ወደፊትም በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሌሎች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በተለያዩ ዘርፎች ተባብሮ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል፡፡ በዙም/Zoom/ የተጀመረው የዘንድሮው Virtual Summer School አውደ-ጥናት ለተከታታይ አምስት ቀናት የሚቀጥል ሲሆን ቀጣይ በሚኖረው የመዝጊያ ስነ-ስርዓት ላይ ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ከሙያ ማህበሩ ጋር ወደፊት በሚሰራባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡


