ፍራንሲስ ጂ. ኮስኮ ፋውንዴሽን ለጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የኮቪድ-19 መከላከያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ፡፡

ዋና መስሪያ ቤቱን በካናዳ ያደረገውና “ትምሕርት ለለውጥ” (Education for Change) በሚል መሪ ቃሉ የሚታወቀው ፍራንሲስ ጂ. ኮስኮ ፋውንዴሽን (ኤፍ.ጂ.ሲ.ኤፍ) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኮሮና ቫይረስን ለመዋጋት እያደረገ ያለውን ጥረት የሚያግዙ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል፡፡ የተደረገው ድጋፍ አስራ አንድ የሚሆኑ የተለያዩ ራስን መጠበቂያና ኮሮና ቫይረስን መከላከያ የቁሳቁስ ዓይነቶችን ያካተተ ሲሆን ከነዚህም መካከል የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብሎች፣ የእጅ ጓንቶች፣ የዓይን መነፅሮች፣ ጫማዎች እንዲሁም ከእጅ ንክኪ ነፃ የሆኑ የእጅ መታጠቢያዎች ይገኙበታል፡፡ የፋውንዴሽኑ የአማራ ክልል አስተባባሪ አቶ አብዮት አሸናፊ የተደረገው ድጋፍ በገንዘብ ሲተመን ከብር 230,000.00 (ሁለት መቶ ሰላሳ ሺህ) በላይ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሕክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ዋና ስራ አስፈፃሚ ዳይሬክተር ፕ/ር የሺጌታ ገላው ኤፍ.ጂ.ሲ.ኤፍ ለጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተለያዩ ጊዜያት እያደረገ ላለው ድጋፍ አመስግነው የተደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ ኮሌጁ በሆስፒታሉ ስር በሚሰሩ ታታሪ ሰራተኞቹ አማካይነት ኮቪድ-19ን ለመዋጋት እያደረገ ላለው ስራ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደሚያደርግ አብራርተዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማሕበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ተስፋየ ሽፈራው ኤፍ.ጂ.ሲ.ኤፍ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ ሕብረተሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ድግፎችን ለመስጠት እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎች መሰል ተቋማት በአብነት የሚጠቀስ እንደሆነ ጠቅሰዋል፡፡ በተለይም ጥራታቸው የጠበቁ ትምሕርት ቤቶችን በመገንባትና በመሠረተ-ልማት ግንባታ እንዲሁም መምህራንን በማሰልጠን “ትምሕርት ለለውጥ” ብሎ የተነሳበትን ዓላማ በተግባር እያሳየ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በድጋፍ ርክክቡ መርሐ-ግብር ላይ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበበ ግዮን ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በተጨማሪ ለባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ትምሕርትና ጤና መምሪያዎች ተመሳሳይ የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል፡፡

Contact CMHS

College Of Medicine and Health Sciences

Bahir Dar University

 Bahir Dar, Ethiopia

Phone:- +251-0582-9 99275

P.o.box:- 79

e-mail:- collegehealthscience@gmail.com

Institutes

Website Design and Developed by LTTU,ICT Copyright © 2017- Bahir Dar University