የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የመጀመሪያውን የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በይፋ አስመረቀ
13 Jan, 2026
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ (ጥር 1፣ 2018 ዓ.ም) - የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ (ESA) ከተመሠረተ 15 ዓመታት በኋላ ከአዲስ አበባ ውጭ የመጀመሪያ የሆነውን የክልል ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፣ በኢትዮጵያ ጨርቃጨርቅና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት (EiTEX) ውስጥ በዛሬው ዕለት መርቆ ስራ አስጀምሯል። ይህ የባሕር ዳር ቻፕተር ጽሕፈት ቤት በኢንስቲትዩቱ ግቢ ውስጥ በሚገኘውና ለተማሪዎች፣ ለምሁራንና ለተመራማሪዎች ምቹ አገልግሎት በሚሰጠው ዘመናዊው "ግሪን ዲጂታል ላይብረሪ" ውስጥ ተደራጅቶ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል።
በምርቃቱ ሥነ-ሥርዓት ላይ የአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ፕ/ር ተከተል ዮሐንስና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር መንገሻ አየነ የጽሕፈት ቤቱን ቁልፍ በመረካከብና ሪቫን በመቁረጥ በጋራ መርቀው የከፈቱ ሲሆን፣ በዕለቱም የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣ የአካዳሚው አባላት የሆኑ ፕሮፌሰሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚደንት ዶ/ር መንገሻ አየነ በምርቃቱ ወቅት ባደረጉት ንግግር፣ አካዳሚው የመጀመሪያውን ቅርንጫፍ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መክፈቱ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር ገልጸው ዩኒቨርሲቲው ከአካዳሚው ጋር በቅንጅት በመሥራት ለአማራ ክልልም ሆነ ለሀገራዊና ዓለም አቀፋዊ የሳይንስ እድገት የሚጠበቅበትን ከፍተኛ አስተዋጽኦ ለመወጣት ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል። ፕሬዚደንቱ አክለውም በአሁኑ ወቅት በዩኒቨርሲቲው ውስጥ 11 የአካዳሚው አባል የሆኑ ፕሮፌሰሮች ቢኖሩም፣ ተቋሙ ካሉት 43 ፕሮፌሰሮችና ከ850 በላይ ረዳት ፕሮፌሰሮች አንጻር ይህ የተደራጀ አቅም ለሀገርና ለሕዝብ ጠቃሚ የሆኑ ሳይንሳዊ ሥራዎችን ለማከናወን ትልቅ ዕድል መሆኑን አብራርተዋል።
የአካዳሚው ሥራ አስፈጻሚ ፕ/ር ተከተል ዮሐንስ በበኩላቸው፣ አካዳሚው በስድስት የሳይንስ ዘርፎች ማለትም በኢንጅነሪንግ፣ በጤና፣ በተፈጥሮ ሳይንስ፣ በጥበባት ዘርፎች ሁሉ ከፍተኛ የምርምርና የማማከር ሥራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን አስታውሰዋል። አካዳሚው ተደራሽነቱን ለማስፋት ባደረገው እንቅስቃሴ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቀዳሚውን ሚና በመውሰድ ደረጃውን የጠበቀ የጽሕፈት ቤት አገልግሎት በማመቻቸቱ የተሰማቸውን ኩራት ገልጸዋል።
ፕ/ር ተከተል አክለውም አካዳሚው ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በቅርበት በመሥራት በሀገራዊ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሳይንሳዊ ምላሾችን እንደሚሰጥና በማማከር፣ በመገምገምና አዳዲስ ሳይንሳዊ እሳቤዎችን በማመንጨት በኩል የላቀ ሚና እየተጫወተ እንደሚገኝ ገልጸዋል። በመጨረሻም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሚገኙና ተፈላጊውን መስፈርት የሚያሟሉ ምሁራን የአካዳሚው አባል በመሆን ሙያዊ ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።



