
ለህፃናት የብስክሌት ስልጠና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
04 Sep, 2025
ለህፃናት የብስክሌት ስልጠና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ በክረምት ስፖርት መቆያ መርሃ ግብር ለህፃናት የብስክሌት ስልጠና መስጠት መጀመሩን አስታውቋል።
ስልጠናውን እየመሩ ያሉት የስፖርት አካዳሚ ተመራማሪና መምህር ዶ/ር ዘመኑ ተሾመ እንደገለጹት፣ ዩኒቨርሲቲው በየክረምት የተለያዩ ስፖርቶችን ለህፃናት ሲያሰለጥን የቆየ ሲሆን፣ በዘንድሮው ዓመት ግን የብስክሌት ስልጠና ለመጀመሪያ ጊዜ መጀመሩን ተናግረዋል።
ዶ/ር ዘመኑ አክለውም የብስክሌት ስልጠናው ባሕር ዳር ከተማን የሚመጥኑ ብስክሌተኞችን ለማፍራት ያለመ ነው ብለዋል። በተጨማሪም፣ ሙያዊ ስልጠና የወሰዱ ወጣት አትሌቶችን በማሰልጠን በአገር አቀፍና በአለም አቀፍ ደረጃ የሚወዳደሩ ብስክሌተኞችን ለማፍራት እንደሚረዳ ገልፀዋል።
በስልጠናው ላይ የተሳተፉ ህፃናትም ስልጠናውን በደስታ እየተከታተሉ ነው። የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ከዚህ ቀደም በተለያዩ የኳስ ጨዋታዎች፣ በሜዳ እና ጠረጴዛ ቴኒስ፣ በአትሌቲክስ እና ማርሻል አርትስ ስልጠናዎችን ሲሰጥ ቆይቷል።

