ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል ብድር ስምምነት ተፈራረሙ
30 Jan, 2026
[ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፤ ጥር 21/2018ዓ/ም ] የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባህር ዳር ዲስትሪክት ጋር በመተባበር ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የሚውል የ"ሲቢኢ በእጀ" (CBE Be-Eje) የዲጂታል ብድር እና ቁጠባ አገልግሎት ስምምነት በይፋ ተፈራርሟል። ይህ ስምምነት በተለይ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች ስልካቸውን በመጠቀም የፋይናንስ አገልግሎቶችን በቀላሉ እንዲያገኙ ለማስቻል ያለመ ነው።
የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ በፊርማ ስነ-ስርዓቱ ላይ እንደገለጹት፣ ባንኩ ያመቻቸው ይህ የዲጂታል ብድር አሰራር ሰራተኞች ለሚያጋጥማቸው አነስተኛ የገንዘብ እጥረት ከሰው ከመበደር ይልቅ ስልካቸውን ተጠቅመው ችግራቸውን እንዲፈቱ ያደርጋቸዋል። ፕሬዚዳንቱ አክለውም ባንኩ ከዚህ የዲጂታል ብድር ባሻገር ለዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የቤት መስሪያ እና የመኪና ብድር አገልግሎቶችን በማመቻቸት ሰፊ የብድር ማዕቀፍ እንዲዘረጋ ጥያቄ እና ሀሳብ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የባሕር ዳር ዲስትሪክት ሀላፊ አቶ ደሞዜ ባለቤ ባንኩ ከዚህ ቀደም ትኩረቱን በግዙፍ የመንግስት ፕሮጀክቶች የፋይናንስ ድጋፍ ላይ አድርጎ የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን የህብረተሰቡን ፍላጎት መሰረት በማድረግ ወደ ግለሰቦች መውረዱን ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ አባላት ባንክ ቤት በአካል መሄድ ሳያስፈልጋቸው በእጅ ስልካቸው ብቻ በመጠቀም ለድንገተኛ ችግሮች እና ለአነስተኛ የሸማች ፍላጎቶች የሚውል ብድር ማግኘት እንደሚችሉ አረጋግጠዋል።
ይህ የዲጂታል ብድር አገልግሎት ከመደበኛው የብድር አሰራር በተሻለ እና ተመጣጣኝ በሆነ የወለድ ተመን የቀረበ መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ስምምነቱ በሁለቱ ተቋማት ከፍተኛ አመራሮች በዶ/ር መንገሻ አየነ እና በአቶ ደሞዜ ባለቤ ፊርማ በይፋ ጸድቋል።

