
የኢትዮጵያ ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ተመሠረተ - ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም የፎረሙ መስራች አካል ነው
Campus Name
21 Jul, 2025
የኢትዮጵያ ምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም ተመሠረተ - ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም የፎረሙ መስራች አካል ነው
የኢትዮጵያ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ፎረም በትምህርት ሚኒስቴር በተሰጠው እውቅና መሰረት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ 8ቱ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎችና 2ቱ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲዎች በጋራ ያቋቋሙት መድረክ ነው።
ይህ ፎረም በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት፣ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ አፄ ቴዎድሮስ ስታዲየም በተዘጋጀው ታሪካዊ ስነስርዓት ላይ ዛሬ ሐምሌ 13 ቀን 2017 ዓ.ም. በይፋ ተመስርቷል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ወክለው የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ተወካይ አቶ አራጋው ብዙአለም በዚሁ የምስረታ ስነስርዓት ላይ ተገኝተዋል።
በምስረታ ስነስርዓቱ ላይ ከተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ፕሬዚዳንቶችና ተወካዮች፣ የዩኒቨርሲቲው የቀድሞ ምሩቃን፣ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የኃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር አስራት አፀደወይን የፎረሙ ሰብሳቢ ሆነው የተመረጡ ሲሆን፣ በመክፈቻ ንግግራቸውም የፎረሙን ዓላማ እና አስፈላጊነት በዝርዝር አብራርተዋል። ዶ/ር አስራት የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች ችግር ፈቺ ምርምሮችን በማከናወን፣ የማህበረሰብ አገልግሎት በመስጠት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች ላይ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸው አበክረው ገልጸዋል።
ይህ ፎረም እንደ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ላሉ የምርምር ተቋማት እውቀትን ለመጋራት፣ የጋራ ምርምሮችን ለማካሄድ እና የሀገሪቱን የልማት ጥረቶች በምርምር ውጤቶች ለመደገፍ ትልቅ አስተዋፅኦ ይኖረዋል ተብሎ ይጠበቃል።
