ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ መንግሥት የዋንጫ ሽልማት ተበረከተለት

30 Sep, 2025

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከክልሉ መንግሥት የዋንጫ ሽልማት ተበረከተለት

መስከረም 19/2018 ዓ/ም (ባሕር ዳር): ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በ2017 ዓ/ም የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ ብሔራዊ ፈተና ያስፈተናቸውን ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ (100%) በማሳለፉ ከአማራ ክልል መንግሥት የላቀ የዋንጫ ሽልማት ተበረከተለት።

ይህ ክብር የተጎናጸፈው በተለይ የዩኒቨርሲቲው ስቲም (STEM) ማዕከል ባስመዘገበው አስደናቂ ውጤት ነው።

የሽልማት ሥነ-ሥርዓቱ ዛሬ መስከረም 19/2018 ዓ/ም በባሕር ዳር ከተማ የተካሄደ ሲሆን፣ የዋንጫ ሽልማቱን ለዩኒቨርሲቲው ያስረከቡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አብዱ ሁሴን ናቸው።

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስቲም ማዕከል ለብሔራዊ ፈተና ካስፈተናቸው 41 ተማሪዎች ውስጥ፣ ሁሉም ተማሪዎች ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚያስገባቸውን ከፍተኛ ነጥብ በማስመዝገብ 100% የማለፍ ውጤት አስመዝግበዋል።

ከ41 ተማሪዎቹ ውስጥ 26 ተማሪዎች ደግሞ ከ500 በላይ ውጤት በማስመዝገብ በክልሉ አብላጫ ውጤት ካስመዘገቡ ተማሪዎች ተርታ ተሰልፈው ከክልሉ መንግሥት ሽልማትና ዕውቅና ተበርክቶላቸዋል።

በአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ የተዘጋጀው ይህ የሽልማትና የዕውቅና መርሃግብር፣ ከ500 በላይ ውጤት ላስመዘገቡ ተማሪዎች የገንዘብ ሽልማት እና 100% የማለፍ ውጤት ላመጡ 7 ልዩ ትምህርት ቤቶችም የዋንጫና የምስክር ወረቀት ሽልማት ተበርክቷል።

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ!

imageimageimage