
የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመረቀ
Poly Campus
21 Jun, 2025
Event Content
የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን ተማሪዎች በዛሬው ዕለት አስመረቀ
[June 21, 2025 Bahir Dar, ISC/BiT]
*******************************
(ሰኔ 14/ 2017 ዓ.ም ISC/BiT) ባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በመደበኛው መርሃ-ግብር በተለያዩ የትምህርት መስኮች ያስተማራቸውን አምስት መቶ ዘጠና (590) ተማሪዎችን በዛሬው ዕለት አስመረቀ፡፡ ከተመራቂዎቹ መካከል 466 የመጀመሪያ ዲግሪ ተማሪዎች ሲሆኑ፤ 118 ተማሪዎችን በሁለተኛ ዲግሪ እና 06 ተማሪዎች በሶስተኛ ዲግሪ በመደበኛው ፕሮግራም ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ ናቸው። በምረቃ መርሃ ግብሩ ላይ የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ፣ የዕለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ዶ/ር አሕመዲን መሐመድ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የከተማና መሰረተ ልማት ዘርፍ አስተባባሪ፣ የተመራቂ ቤተሰቦች፣ ሌሎች የፌደራል እና የክልል የክብር እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
ዶ/ር መንገሻ አየነ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞዎችን የባሕር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት እና የባሕር ዳር መምሕራን ኮሌጅ በማዋሃድ በግንቦት ወር 1992 ዓ.ም በዩንቨርስቲነት እንደተቋቋመ ገልፀው አሁን ላይ በአፍሪካ ቀዳሚ የምርምር እንዲሁም በኢትዮጵያ ግንባር ቀደም ተመራጭ ዩኒቨርሲቲ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በመቀጠልም የBiTec ቢዝነስ ማስጀመሪያ ምህዳሮቻችን (startup ecosystems) እና በብሔራዊ ABIC2024 ሽልማትን ያገኙት የንግድ ሀሳቦቻችን ለቴክኖሎጂ ፈጠራ እና ለኢንተርፕራይዝ ልማት የሚደረገውን የቁርጠኝነት ጉዞ ማሳያ ናቸው ብለዋል።ተመራቂ ተማሪዎች ስራ ፈጣሪ፣ መሪዎች እንዲሁም ኢትዮጵያን እና አፍሪካን የሚያሻግር ራዕይ ሰናቂ ፋና ወጊዎች እንዲሆኑ አሳስበዋል። ወደ ስራው አለም ሲገቡም በጉጉት መማርን፣ በእውቀትና በድፍረት መምራትን እና በታማኝነት ማገልገልን ዕሴት ሊያደርጉ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ለመውጫ ፈተና ካስቀመጣቸው 420 ተማሪዎች መካከል 417 ተማሪዎች የማለፊያ ነጥብ ማስመዝገባቸውን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ ገልፀዋል፡፡ አክለውም ኢንስቲትዩቱ በዳታ ሳይንስ እና በሳይበር ደህንነት ለመጀመሪያ ለመጀመሪያ ጊዜ በመጀመሪያ ዲግሪ ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች እያስመረቀ መሆኑን ተናግረዋል፡፡፡
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከየፋኩልቲያቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ተመራቂ ተማሪዎች የሜዳሊያ ተሸላሚ ሲሆኑ ከአጠቃላይ የኢንስቲትዩቱ እና ከአጠቃላይ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ተመራቂ ተማሪወች መካከል የኮምፕዩቲንግ ፋኩልቲ የሳይበር ደህንነት (Cyber Security) ተማሪ የሆነችው ፌቨን ጉርጁ 4 ነጥብ በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ ሆናለች፡፡
Information and Strategic Communication Directorate
Facebook፡-- https://www.facebook.com/bitpoly
Telegram፡- https://t.me/bitpoly
Website፡- https://www.bdu.edu.et/bit
Twitter: - https://twitter.com/BiT_BDU