ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ቦይንግ የአቪዬሽን ፈጠራ ማዕከል ለማቋቋም የረጅም ጊዜ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 1፣ 2018 ዓ.ም. /ISC/BiT]
Poly Campus
23 Jun, 2026
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ቦይንግ የአቪዬሽን ፈጠራ ማዕከል ለማቋቋም የረጅም ጊዜ የትብብር ስምምነት ተፈራረሙ
ባሕር ዳር፣ ሐምሌ 1፣ 2018 ዓ.ም. /ISC/BiT]
*******************************************************************************************
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እና ቦይንግ [NYSE: BA] በኢትዮጵያ በፍጥነት እያደገ የሚገኘውን የአቪዬሽን ዘርፍ ለማጠናከር፣ በኤሮስፔስ ምህንድስና ትምህርት ፈጠራን ለማበረታታት፣ እንዲሁም ብቁ የሰው ኃይል ለማፍራት ያለመ የረጅም ጊዜ የትብብር ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስታወቁ።
በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የቦይንግ አፍሪካ ዋና ዳይሬክተር ሄኖክ ተፈራ ሻውል እንደገለጹት "በሚቀጥሉት ሁለት አስርት ዓመታት ውስጥ የአፍሪካ አየር መንገዶች ከ1,200 በላይ አዳዲስ አውሮፕላኖችን እና ከ74,000 የሚበልጡ አዲስና ተጨማሪ የአቪዬሽን ባለሙያዎች ያስፈልጋቸዋል። ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ተሰጥዖ ላላቸው ወጣቶች ግልጽ የሙያ እድገት መንገዶችን እንፈጥራለን፣ ትምህርትን ከኢንዱስትሪው ፍላጎት ጋር እናጣጥማለን፣ እንዲሁም የኢትዮጵያን አየር መንገድ አገልግሎቶች፣ የአየር ማረፊያ መሠረተ ልማቶች እና የኤሮስፔስ አካላት ማምረቻ ኢንዱስትሪ እየተስፋፋ ያለውን እድገት እንደግፋለን።" ብለዋል።
ይህ ትብብር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ውስጥ የአቪዬሽን ፈጠራ ማዕከል (Aviation Innovation Center) እንዲቋቋም ድጋፍ ያደርጋል። ማዕከሉ በተግባር ላይ የተመሰረተ ትምህርት፣ ምርምር፣ ፈጠራ፣ እንዲሁም ለጀማሪ የቴክኖሎጂ እና የፈጠራ ሥራዎች የድጋፍና የማብቃት (Incubation) ማዕከል ሆኖ ያገለግላል።
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር መንገሻ አየነ እጅጉ በበኩላቸው ትብብሩን “ታሪካዊ ምዕራፍ” ብለው የገለጹ ሲሆን "ከቦይንግ ጋር የጀመርነው የሁለትዮሽ ትብብር ለባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስፈላጊና ታሪካዊ ሲሆን ተቋማቱ በጋራ በመስራት በኤሮስፔስ ትምህርት፣ በምርምር፣ ፈጠራ እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ዘርፎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ማዕከል ለመገንባት በጋራ እንሰራለን። ይህም የወደፊቱን የአቪዬሽን ባለሙያዎች ለማፍራት እና በዩኒቨርሲቲዎችና በኢንዱስትሪው መካከል ያለውን ትብብር ለማጠናከር ያገለግላል ብለዋል። ይህ ማዕከል በባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት ያለውን የምህንድስና አቅም መሠረት በማድረግ፣ የብቁ የሰው ኃይል ልማትን፣ የቴክኖሎጂ ንግዳዊነትን እና የኤሮስፔስ ፈጠራን የሚያፋጥን ማዕከል ይሆናል። በዚህ አጋርነት ኢትዮጵያ እያደገ የሚገኘውን የኤሮስፔስ ሥነ-ምህዳር በመደገፍ፣ ለአገራዊና ለአካባቢያዊ ኢንዱስትሪ ሽግግር አስተዋፅኦ ለማድረግ ቁርጠኞች ነን ።" ብለዋል።
በእ.ኤ.አ. 2026 ትብብሩ በዋናነት የአቪዬሽን ፈጠራ ማዕከሉን መሠረተ ልማት በማሟላት፣ የላቦራቶሪ መሣሪያዎችን በማቋቋም እና በዘርፉ ብቁ ባለሙያዎችን ማፍራት ላይ ያተኩራል። ማዕከሉ ለተማሪዎች እንደ 3ዲ ፕሪንተሮች፣ የበረራ ሲሙሌተሮች፣ የዲዛይን ሶፍትዌሮች፣ የድሮን መገጣጠሚያ ኪቶች እና የአቪዮኒክስ መፈተሻ መሳሪያዎችን ጨምሮ ዘመናዊ መሣሪያዎችን ያቀርባል። እነዚህ መሣሪያዎች ወጣት መሐንዲሶች ዲጂታል መፍትሔዎችን፣ ዘላቂ የአቪዬሽን ስርዓቶችን፣ አዳዲስ የኤሮስፔስ ደረጃ ቁሳቁሶችን እና ሰው-አልባ አየር ተሽከርካሪዎችን (UAV) እንዲነድፉ፣ እንዲሞክሩና እንዲያሻሽሉ ያስችላቸዋል። ከዚህም በተጨማሪ ማዕከሉ ለሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች፣ ለ2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች እና በኢትዮጵያ ለሚገኙ የኤሮስፔስ ስታርትአፕ ድርጅቶችም ክፍት ይሆናል።
በተጨማሪም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና በቦይንግ መካከል የተጀመረው ትብብር፣ በፈጠራ ውድድሮች፣ በሙያ ማጎልበቻ ወርክሾፖች እና የመካሪነት (Mentorship) መርሃ ግብሮች አማካኝነት የተማሪዎችን የመማር ልምድና ተሳትፎ የበለጠ ያጠናክራል።
ይህ ትብብር ቦይንግ በኢትዮጵያ ውስጥ በሂሳብና ሳይንስ (STEM) ትምህርት እና በሰው ኃይል ልማት የሚያካሂደውን ቀደም ሲል የተጀመረ ተግባር ያጠናክራል፤ ባለፉት አምስት ዓመታትም ከ14,700 በላይ ወጣቶችን ተጠቃሚ አድርጓል።
የሁለቱ ተቋማት አጭር መረጃ
ቦይንግ አፍሪካ
ቦይንግ ዓለም አቀፍ የኤሮስፔስ ኩባንያ ሲሆን የንግድ አውሮፕላኖችን፣ የመከላከያ ምርቶችን እና የስፔስ (ጠፈር) ስርዓቶችን ከ150 በላይ አገሮች ይዘረጋል፣ ያመርታል እንዲሁም አገልግሎት ይሰጣል። ቦይንግ በአፍሪካ የአቪዬሽን እድገት ከ70 ዓመታት በላይ ተሳትፎ አለው፣ በአፍሪካ የንግድ አቪዬሽን ገበያ ውስጥም 70% ድርሻ ይይዛል። ኩባንያው በኢትዮጵያ እና በደቡብ አፍሪካ ቢሮዎች አሉት፣ በአፍሪካ ዙሪያም ከአየር መንገዶች ጋር ተያያዥ የቴክኒክ ባለሙያዎች ይገኛሉ። ባለፉት አሥርት ዓመታት ቦይንግ በአፍሪካ የወጣቶች ፕሮግራም ውስጥ 14.5 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት አድርጓል፣ ባለፉት አምስት ዓመታትም ከ58,500 በላይ ሰዎችን ተጠቃሚ አድርጓል። ለተጨማሪ መረጃ https://www.boeing.africa ይጎብኙ።
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ (BDU) በኢትዮጵያ ካሉ ከፍተኛ የምርምር ዩኒቨርሲቲዎች መካከል አንዱ ሲሆን በትምህርት፣ በምርምር፣ በፈጠራ እና በማህበረሰብ አገልግሎት የላቀ ብቃት ያለው ተቋም ነው። ዩኒቨርሲቲው በአሁኑ ወቅት ከ25,970 በላይ ተማሪዎችን በ451 የትምህርት መርሀግብሮች እያስተማረ ሲሆን 113 የመጀመሪያ ዲግሪ፣ 187 የሁለተኛ ዲግሪ እና 115 የሦስተኛ ዲግሪ መርሀግብሮች እያስተማረ ይገኛል። ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 18 አካዳሚክ ክፍሎች፤ 5 ኮሌጆች፣ 5 ኢንስቲትዩቶች፣ 2 ፋኩልቲዎች፣ 3 ትምህርት ቤቶች እና 3 አካዳሚዎች አሉት። በተጨማሪም 13 የምርምር ማዕከላት ያሉት ሲሆን እነዚህ ማእከላት ሳይንሳዊ ምርምርን፣ የቴክኖሎጂ ልማት እና ፈጠራን ያጠናክራሉ።
Information and Strategic Communication Office
Facebook፡-- https://www.facebook.com/bitpoly
Telegram፡- https://t.me/bitpoly
Website፡- https://www.bdu.edu.et/bit
Twitter: - https://twitter.com/BiT_BDU
LinkedIn: - https://www.linkedin.com/company/bitpoly/






