"Leadership Role in Quality Culture" ስልጠና

"Leadership Role In Quality Culture"
በሚል ርዕስ ዙሪያ ስልጠና ተሰጠ
በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ጥራት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት አዘጋጅነት "Leadership Role in Quality Culture" በሚል ርዕስ ዙሪያ ከሁሉም ግቢ ለተውጣጡ የዩኒቨርሲቲው አመራሮችና መምህራን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ በሆኑት በፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው በጥበብ ሕንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በ01/11/14 ዓ.ም ስልጠና ተሰጠ፡፡
 
ስልጠናውን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ ለአሰልጣኙና ለመላው ታዳሚ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ጥራት የዩኒቨርሲቲው መገለጫ ከሆኑት ዋና ዋና እሴቶች አንዱ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
 
ፕሬዘዳንቱ በማስከተል ከሌሎች ልቆ ለመገኘት በእውቀት ላይ የተመሰረተ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እና በሀገራችን ብሎም ከዓለም ሀገራት ጋር ተወዳዳሪ ለመሆን ተቋማችን በማሪታይም አካዳሚ፣ በባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት፣በኢትዮጲያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ እንዲሁም በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ የተሰሩ ስራዎች እና የተሰጣቸው እውቅና ዩኒቨርሲቲውን ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ እንደሚያደርገው አስገንዝበዋል፡፡
 
ዶ/ር ፍሬው አክለውም ዩኒቨርሲቲው በአጭር ጊዜ ውስጥ ከ72 በላይ ስማርት ቦርድ በማስመጣትና በርካታ ስማርት የመማሪያ ክፍሎች በማዘጋጀት፣አዳዲስ ህንፃዎችን በማስገንባት፣በሁሉም ግቢዎች የተሰሩት የምድረ ውበት ስራዎች የጥራት መገለጫዎች እንደሆኑና ለሌሎች ተቋማት በሞዴልነት የሚታዩ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡ በተጨማሪም በመማር ማስተማሩም ሆነ በምርምሩ ከወትሮው በተለዬ መልኩ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመገኘት ጥራትን መሰረት አድርጎ መስራት አስፈላጊ በመሆኑ ቀሪ ክፍተቶችን ለመሙላት ስልጠናው ጉልህ ፋይዳ ስላለው ሁሉም የተቋሙ መምህራን ትኩረት ሰጥቶ እንዲከታተልና በተግባር ላይ እንዲያውለው ፕሬዘዳንቱ አሳስበዋል፡፡
 
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አጠቃላይ ጥራት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶ/ር አንዳርጋቸው ሞገስ በበኩላቸው የስልጠናው ዓላማ በዩኒቨርሲቲው በርካታ አኩሪ ተግባራት እየተከናወኑ ስለሆነ ሁሉም ስራ በጥራት የተደገፈ ለማድረግ ታልሞ በዩኒቨርሲቲው በሁሉም ግቢዎች ያሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ዲኖች፣ም/ዲኖችና ከኮርስ ቸሮችን ጨምሮ እስከ ትምህርት ክፍል ተጠሪ ድረስ ላሉ የስራ ኃላፊዎች እንደተሰጠ አውስተዋል፡፡ አክለውም ሰልጣኞች ያገኙትን ክህሎት ለሌሎችም በማካፈል ተደራሽነቱ እንዲሰፋ በማሰብ ስልጠናው መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡
እንደ ዳይሬክተሩ ጥራት ከሌሎች ከፍ ብሎ ለመገኘት አንኳር ጉዳይ ስለሆነ አሰልጣኙ በሙያው የካበተ ልምድ ስላላቸው ሰልጣኞች በርካታ ክህሎት እንደሚያገኙና ለወደፊት ሁሉም የስራ ኃላፊ በእቅድ ውስጥ በማስገባት ጥራትን መሰረት ያደረገ ስራ በዩኒቨርሲቲው እንዲሰፍን አሳስበዋል፡፡
 
አሰልጣኙ በውጭም ሆነ በአገር ውስጥ ስለጥራት ምንነትና አስፈላጊነት የካበተ ልምድ ያላቸው እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ጥራት የውጭም ሆነ የውስጥ ደንበኛን ለማርካት ፋይዳው የጎላ ስለሆነ በጥራት ቀድሞ መገኘት ተገቢ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
 
ፕሮፌሰሩ በማስከተል በጥራት ዙሪያ ያለው ውድድር የርዕስ በርዕስ ሳይሆን ዓለም አቀፍ መሆኑን አስገንዝበው ዩኒቨርሲቲው ጥራት ያለው ተማሪ ለማፍራት ጥራት ያለው መምህር ሊኖረው እንደሚገባ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡
 
የስልጠና አሰጣጣቸውም በፅሁፍና በተንቀሳቃሽ ምስል የተደገፈ በመሆኑ ተሳታፊዎች ስልጠናው ጥሩና ደረጃውን የጠበቀ መሆኑን ገልፀው በርካታ ነገር መቅሰማቸውን ተናግረዋል፡፡ አሰልጣኙ ባቀረቧቸው ፅሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሂዶ ለተነሱት ጥያቄዎች መልስ ተሰጥቶባቸዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አካዳሚክ ጉዳዩች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ በማጠቃለያ ንግግራቸው ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ወርቃማ ጊዜአቸውን ሰጥተው ይህን ዘርፈ ብዙ ስልጠና በመስጠታቸው ከፍ ያለ ምስጋና አቅርበው ዩኒቨርሲቲው ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ እንደሚገኝ አውስተው ካለው ከፍ ብሎ ለመገኘት ከስርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ጥራት ያለው ስራ በማከናወንና ከሌሎች ቀድሞ በመገኘት እንዲሁም ተማሪዎች መርጠው እንዲመጡ ለማድረግ ሁሉም ከስልጠናው ያገኘውን ክህሎት ወደ ተግባር እንዲለውጥ በአደራ መልኩ አሳስበዋል፡፡
በሙሉጎጃም አንዱዓለም