8ኛው አገር አቀፍ የቋንቋ፤ባህልና ስነ-ተግባቦት ዐውደ-ጥናት

8ኛው አገር አቀፍ የቋንቋ፤ባህልና ስነ-ተግባቦት ዐውደ-ጥናት ተካሄደ

በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ የሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ አዘጋጅነት 8ኛው አገር አቀፍ የቋንቋ፤ባህልና ስነ-ተግባቦት ዐውደ-ጥናት በዋናው ግቢ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሄደ፡፡

በመርሃ ግብሩ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ ሂዩማኒቲስ ፋኩልቲ ዲን ዶ/ር ሰፋ መካ የጉባኤው መሰረታዊ አላማ ፋኩልቲው ስልጠና በሚሰጥባቸው የቋንቋ፣ የባህል፣ የስነ ፅሁፍ፣ የጋዜጠኝነት እና ስነ ተግባቦት ጥናት ዘርፎች እንዲቀርቡ በማድረግ ግኝቶቹ ህብረተሰቡ እንዲያውቃቸው እና እንዲጠቀምባቸው ምቹ ሁኔታ መፍጠር ሲሆን ቋንቋ፣ ባህል እና ማንነት መልካም አጋጣሚ ወይስ ስጋት በሚል አጠቃላይ ጭብጥ ላይ የተመሰረተ ነው ብለዋል፡፡

 

ዶ/ር ሰፋ አክለውም 8ኛው አገር አቀፍ ዐውደ ጥናት ከቀደሙት ጉባኤዎች በአላማ አንድ ቢሆንም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በተለይም በአገራችን ውስጥ ጎሳን መሰረት ያደረገ ግጭት ጋር በተያያዘ ጠቃሚና ደረጃቸውን የጠበቁ ጥናቶችንና የመፍትሄ ሀሳቦች የቀረቡበት መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው ጠቁመዋል፡፡

አውደ ጥናቱ በአገር አቀፍ ደረጃ የተካሄደ ሲሆን ከዩኒቨርስቲው ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ባሻገር ከሠላም ሚኒስቴር እና ሀገር በቀል ዩኒቨርስቲዎች በመጡ ምሁራንና ተመራማሪዎች የተለያዩ ፅሁፎችን በማቅረብ የተሳተፉበት ነው፡፡

በጉባኤው ባህል፣ ቋንቋ እና ማንነት እንዲሁም ወቅታዊ ፈተናዎች እና እድሎች ዙሪያ መሰረት ያደረጉ ስምንት የጥናት ፅሁፎች የቀረቡ ሲሆን በውይይቱም ተማሪዎች፣ መምህራንና ሰራተኞች እንዲሁም  ጥሪ  የተደረገላቸው  እንግዶች  ተሳትፈዋል፡፡

 

ዘጋቢ፡- ወንዳለ ድረስ