2ኛው የታዳጊ ወንዶች እግር ኳስ ውድድር መካሄድ ጀመረ

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ 2ኛውን የታዳጊ ወንዶች እግር ኳስ ውድድር ማካሄድ ጀመረ

 [ነሐሴ 24/2014 ዓ/ም፤ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ]

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አዘጋጅነት ባሕር ዳር እና አካባቢው የሚገኙ የታዳጊ ወንድ እግር ኳስ ፕሮጀክቶች የሚሳተፉበት 2ኛው የምዘና ውድድር በዩኒቨርሲቲው ስፖርት አካዳሚ በድምቀት መካሄድ ተጀምሯል።

በ15 የፕሮጀክት ተሳታፊ ቡድኖች መካከል የተጀመረው የእለቱ ውድድር ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ከሰባታሚት ቀበሌ አገናኝቷል። በውድድሩም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሳባታሚት አቻውን 5 ለ 1 በሆነ ውጤት በማሸነፉ ድል ቀንቶታል።

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የባሕር ዳር ከተማ የፕሮጀክቶች የምዘና ውድድር አስተባባሪ እና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ታዳጊ ፕሮጀክት አሰልጣኝ አቶ ዳንኤል ጌትነት የውድድሩን አላማ ሲናገሩ አመቱን ሙሉ እግር ኳስ ሲጫወቱ ለነበሩ ህፃናት የውድድር እድል መፍጠር፣ አሰልጣኞች ያላቸውን ጠንካራ እና ደካማ ጎን የሚመዝኑበት፣ ልጆችም የውድድር ልምድ እና ጫናን መቋቋም እንዲችሉ በማድረግ አስተዋፅኦው የጎላ እንደሆነ ገልጸው ውድድሩ እስከ ጳጉሜ 3 ድረስ እንደሚቀጥል ተናግረዋል፡፡

አቶ ዳንኤል ይህ ውድድር ለሁለተኛ ጊዜ የተደረገ ሲሆን በቀጣይ አመት አመቱን ሙሉ በሳምንት ሁለት ቀን እየተጫወቱ ምዘና በማካሄድ ጎን ለጎን ደግሞ ስልጠና ይሰጣቸዋል ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ የእግር ኳስ መምህር እና የአለም አቀፍ እግር ኳስ ዳኛ ዶ/ር ኃይለ እየሱስ ባዘዘው በበኩላቸው ውድድሩ በ15 ክለቦች ከ16 ዓመት በታች የሚደረግ የታዳጊ ወጣቶች እግር ኳስ ውድድር መሆኑን ጠቁመው፤ በከተማው ውስጥ በፕሮጀክት ታቅፈው ለሚሰለጥኑ ከ20 በላይ ክለቦች ቢያንስ በአመት አንድ ጊዜ ከተማው ውስጥ የሚደረገውን የታዳጊዎች መተካካት ሊያግዝ ይችላል በሚል  መጀመሩን ገልፀውልናል፡፡

ዶ/ር ኃይለ እየሱስ ውድድሩ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማሩ ባሻገር ማህበረሰቡን ከማገልገል አንጻር ከ300 በላይ የሚሆኑ ታዳጊ ወጣቶች ክረምቱን በውድድር እንዲያሳልፉ የአካዳሚው መምህራን የዳኝነት ስልጠና በመውሰድ ለታዳጊዎቹ የሚያደርጉት እገዛ አንዱ ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

በባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የአደይ አበባ የፕሮጀክት አሰልጣኝ አቶ ሞገስ ቀለምወርቅ ቡድናቸው በዚህ አመት አማራ ክልል ባዘጋጀው የፕሮጀክት ሙከራ ላይ አራተኛ ሆኖ እንዳጠናቀቀ እና ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ እያካሄደ ባለው ከ16 ዓመት በታች ውድድር እየተሳተፈ ይገኛል ብለዋል፡፡ በዚህ ውድድር ታዳጊዎች በምን ደረጃ እንደሚገኙ የምንመዝንበት የአቋም መፈተሻ እና እኛም አሰልጣኞች ምን ያህል አሰለጠን የሚለውን የምንለካበት ነው ብለዋል፡፡

በውድድሩም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዚደንት ዶ/ር ተስፋዬ  ሽፈራው፣ የባሕር ዳር ከነማ ዋና አሰልጣኝ ኢንስትራክተር አብርሃም መብራቱ፣ ከባሕር ዳር ከተማ እግር ኳስ ፌደሬሽን አቶ ዳግማዊ፣ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዶ/ር ዘላለም እንዲሁም የስፖርት አካዳሚ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ዶ/ር ተከተል በመገኘት ታዳጊ ተወዳዳሪዎችን  በማበረታታት ውድድሩን አስጀምረዋል።

  ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ- ባዳዩ-BDU

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

Wisdom at the source of Blue Nile

Thank you for visiting, inviting and sharing our Pages!

Thank you for your likes and comments!

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Telegram ፡- t.me/BDU_ISC_Official

Facebook: - https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube ፡- www.youtube.com/c/BduEduEt

LinkedIn ፡- www.linkedin.com/school/bahir-dar-university

Twitter: - https://twitter.com/bdueduet

Tiktok:-https://vm.tiktok.com/ZMLgRxdfL

website :- www.bdu.edu.et