የፈጠራና የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸዉ ወጣቶች ተሸለሙ

የተሻለ የፈጠራና የቢዝነስ ሃሳብ ያላቸዉ ወጣቶች ተሸለሙ
************************************************
(ሐምሌ 08/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲBDU)
በባሕር ዳር ዩኒቨርስቲ፣ ኢንዲያና ዩኒቨርሲቲ፣ ደ/ማርቆስ ዩኒቨርሲቲና አይቪ ቴክ ኮሚኒቲ ኮሌጅ ትብብርና በአሜሪካ ኤምባሲ የገንዘብ ድጋፍ እየተተገበረ የሚገኘዉ ፓይቤልት (Partnership in Business Entrepreneurship and leadership Transformation /PIBELT/ ፕሮጀክት በሥራ ፈጠራ ስልጠና ላይ ሲሳተፉ የነበሩ ወጣት ስራ ፈጣሪዎችን በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ህንፃ አዳራሽ ባለድርሻ አካላትና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በተገኙበት ለስራ መጀመሪያ የሚሆን የገንዘብ ሽልማት (Seed money award) ተበረከተ፡፡
በሽልማት ፕሮግራሙ ላይ በመገኘት ስለ ፕሮጀክቱ ማብራሪያ የሰጡት የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዶ/ር ጌታሁን የማታ ፕሮጀክቱ 3 አላማዎችን አንግቦ ይንቀሳቀሳል ብለዋል፡፡ እነዚህም፡
1ኛ.በባሕር ዳር−ደ/ማርቆስ ኮሪደር ያለዉን ኢንተርፕርነርሽፕ ስነ−ምህዳር ማጠናከር፣
2ኛ. የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮችን አቅም መገንባትና
3ኛ. ተቋማዊ ትስስር መፍጠር ዋነኞቹ ናቸዉ ብለዋል፡፡
ዶ/ር ጌታሁን አክለዉም ሽልማቱ ለሁለተኛ ጊዜ የተሰጠ መሆኑን ገልፀዉ በመጀመሪያዉ ዙር 5፣ በዚህ ዙር ደግሞ 6 የቢዝነስ ሃሳብ ላላቸው ወጣቶች እንደተሰጠና ለሁለቱ ዙር ሽልማቶች ከ800,000 ብር በላይ ወጭ ተደርጓል ብለዋል፡፡ ወጣቶቹ ሽልማቱን ከወሰዱ በኋላም ክትትል እናደርጋለን ያሉት ዶ/ር ጌታሁን ፕሮጀክቱ ቢጠናቀቅም በዩኒቨርሲቲዉ በሚገኘዉ የኢንተርፕርነርሽፕ ልማትና ማበልፀጊያ ማዕከል በኩል ክትትሉ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
የኢንተርፕርነርሽፕ ልማት እና ማበለጸጊያ ማዕከል (Entrepreneurship Development and Incubation Center- EDIC) ማዕከል ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘዉዱ ላቀ በበኩላቸዉ ማዕከሉ ከሚሰጣቸው የስራ ፈጠራና ተያያዥ የስልጠና ዘርፎች ዉስጥ የንግድ ልማት ስልጠናና ምክር፤ የስራ አመራር ስልጠናና ምክር ወ.ዘ.ተ. በተጨማሪ ከልዩ ልዩ ተቋማት ጋር በጋራ ዘላቂ የስራ ፈጠራ ምህዳር (Sustainable entrepreneurship ecosystem) ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን እንስተዋል፡፡ ማዕከሉ ልዩ ልዩ የስራ ፈጠራ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ለዩኒቨርስቲው ተማሪዎች፤ ለተመረቁ ተማሪዎች፤ ለመምህራንና አስተዳደር ሰራተኞች፤ እንዱሁም ለአካባቢው ወጣቶችና የንግድ ማህበረሰብ ስልጠናና ምከር አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አብራተዋል፡፡
ማዕከሉ የዩኒቨርሰቲውን ተደራሽነትና ራዕይ ለማሳካትም በፈጠራና አለማቀፋዊነት (Innovation and Internationalization) ረገድም ጉልህ ሚና እንዳለውና ድርሻውንም እየተወጣ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የዉጭፕሮጀክቶች ኃላፊና የፕሮጀክቱ አስተባባሪ አቶ ገበየሁ መንገሻፕ ሮጀክቱ ለሁለት ዓመታት የትግበራ ስራ ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡
በዩኒቨርሲቲዉ እየተተገበሩ ካሉ ዉጤታማ ፕሮጀክቶች በቀዳሚነት ከሚጠቀሱ አንዱ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ገበየሁ ፕሮጀክቱ ለወጣቶቹ ተከታታይ ስልጠና የሰጠ ሲሆን ለወጣቶቹ የስራ መስሪያ ቦታ እና ልዩ ልዩ ድጋፎችን እንዲያገኙ ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብረዉ እንዲሰሩ የማስተሳሰር ስራ ዩኒቨርሲቲዉ እየሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በአሜሪካ ኤምባሲ የገንዘብ ድጋፍ የሚንቀሳቀሰዉ ይህ ብሮጀክት ከ20 ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ዉስጥ በዚህ ዙር ለ6ቱ ለስራ መጀመሪያ ሊሆን የሚችል 403,600 ብር የማበረታቻ ሽልማት ሰጥቷል፡፡
በሽልማት ስነ−ስርዓቱ ላይ ተገኝተዉ የማበረታቻ ሽልማቱን የሰጡት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈራዉ ለተሸላሚዎች ባስተላለፉት መልዕክት “ሽልማቱ ዘር ነዉ፤ዘር ደግሞ አይበላም” ስለሆነም ይህንን እርሾ ይዛችሁ ቢዝነሳችሁን እንዲታሳድጉ እንጅ ለዕለታዊ ፍጆታ እንዳታዉሉት ሲሉ አሳስበዋል፡፡ አዲስ አበባ የሚገኘዉን የአሜሪካ ኤምባሲ በመወከል በዕለቱ መልዕክት ያስተላለፉት አቶ ጌዲዮን ማሞ በበኩላቸዉ የአሜሪካ ኤምባሲ ከሚሰራቸዉ ስራዎች (University Partnership Initiatives-UPI) ፕሮጀክቶች ዉስጥ አንዱ የPIBELT ሲሆን ዉጤታማ ፕሮጀክት መሆኑን እንስተዉ የፕሮጀክቱን ስታፎች አመስግነዋል፡፡ እንዲሁም የስራ ፈጣሪ ወጣቶችን በማመስገን የተሰጣቸዉን የስራ መጀመሪያ ገንዘብ ለተጠቀሰዉ አላማ ማዋል እንደሚገባቸዉና ዩኒቨርሲቲዉም ዘላቂ ክትትልና ድጋፍ ሊያደርግላቸዉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በሽልማት ስነ−ስርዓቱ ላይ በክብር እንግድነት የተገኙት የአማራ ክልል ሳይንስና ቴክኖሎጅ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር አቶ መላኩ ጥላሁን መስሪያ ቤታቸዉ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር በጋራ እንደሚሰራ ገልፀዉ በዩኒቨርሲቲና ኢንዱስትሪ ትስስር ዙሪያ በርካታ ስራዎች እንዲሰሩ እናደርጋን ብለዋል፡፡ አቶ መላኩ አክለዉም የቢዝነስ ሃሳቦቹ ፈቃድ ከሌላቸዉ ፈቃድ እንዲያገኙ እንደሚያድርጉ ለተሸላሚዎች ተናግረዋል፡፡
በእለቱ ከፋይናንስ ተቋማት የተገኙ ተጋባዥ እንግዳዎች ስራ ፈጣሪ ወጣቶች የንግድ ስራቸዉን ለማሳደግ የሚያግዙዋቸዉ ልዩ ልዩ የፋይናንስ ማዕቀፎች መኖራቸዉን የጠቆሙ ሲሆን ስራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለመደገፍ የፕሮጀክት ፋይናንስ እና የሊዝ ማሽን ፋይናንስ እየሰጡ መሆናቸዉን ገልፀዉ ወጣቶቹ የማዕቀፎቹ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አሳስበዋል፡፡ ከላይ ከተገለፁት የፈይናንስ ማዕቀፎች በተጨማሪ በንግድ ሀሳብ ላይ የተመሰረተ (idea financing) የፋይናንስ ማዕቀፍ ለመስጠት በሂደት ላይ መሆናቸዉን ገልፀዋል፡፡
የንግድ ሀሳቦችን በይበልጥ ለማሳደግና ከፋይናንስና የቦታ አቅርቦት በተጨማሪ ስራ ፈጣሪ ወጣቶች ልዩ ልዩ የክህሎት ስልጠና፤ የንድግድ ልማት አገልግሎቶች እና የምክር አገልግሎት በዩኒቨርሲቲዉ የስራ ፈጠራ ማዕከልና በአጋር አካላት ትብብር ቀጣይነት ባለዉ መልኩ እንዲመቻችላቸዉ አሳስበዋል፡፡
በሽልማት ስነ−ስርዓቱም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅት ተወካዮች፣የልማት ባንክና አዋሽ ባንክ ተወካዮች፣የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች በመገኘት ለስራ ፈጣሪዎች ያላቸዉን አጋርነት አሳይተዋል፡፡