የግእዝና የአዝማሪ ዐውደ ጥናት

                       የግእዝና የአዝማሪ ዐውደ ጥናት እየተካሄደ ነው

የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል 5ኛውን ሀገር አቀፍ የግዕዝና የአዝማሪ አውደ ጥናት በዋናው ግቢ እያካሄደ ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ተገኝተው ለተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልእክት ያስተላለፉት የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዐባይ የባህልና ልማት ጥናትና ምርምር ማዕከል ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉቀን አንዷለም  ‹‹ ግዕዝ ውእቱ መጽሔታ ለኢትዮጵያ ዘትሬኢ ኩለንታሃ (ግእዝ ኩለመናዋን የምታይበት የኢትዮጵያ መስታይቷ) የዕለቱ ጭብጥ መሆኑን ጠቁመው በዓሁኑ ስዓት ከ36 ሺ በላይ ቤተ ክርስቲያናት በግዕዝ ቅዳሴ ይከወናል ፣ ቅኔ ይዘረፋል ፤ ስለዚህ የግዕዝ ቋንቋ ሞቷል የሚሉ የስነ ልሳን ትምህርት ምሁራን ሀሳባቸው ስህተት ነው ብለወል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጅክ ኮሚኒኬሽን ምክትል ፕሬዚደንት ዶ/ር ዘውዱ እምሩ  በመርሃ ግብሩ መክፈቻ ተገኝተው  እንደተናገሩት የግዕዝ ቋንቋን ለማሳደግ ምሁራን በችግሮች ዙሪያ የተለያዩ ጥናቶችን በማድረግ ብሎም መፍትሄዎች ላይ ወደ ተግባራዊ እንቅስቃሴ በመግባት ግእዝን በተሸለ መጠቀም እንዲቻል ብዙ ስራ መሰራት አለበት ብለዋል፡፡ ዶ/ር ዘውዱ አክለውም ደኖቻችን እየተመናመኑ ወጥተው በቤተክርስቲያን ቅፅሮች አካባቢ ብቻ ተወስነው እንደመገኘታቸው ሁሉ ግእዝ ቋንቋችንም ሰፈሩ በቤተክርስቲያን ብቻ ተወስኖ መቆየቱ ቋንቋውን በማፋፋት በኩል የተሰሩ ስራዎች አናሳ መሆናቸውን የሚያሳይ ነው ብለዋል፡፡

በዓውደ ጥናቱ የክብር እንግዳ የሆኑት አቶ ሠርፀ ፍሬ ስብሐት በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ም/ኃላፊ በኩላቸው  በበኩላቸው አዝማሪነት የኢትዮጵያን ሙዚቃ በስልታዊ መንገድ እንዲጓዝ ያደረገ ባለውለታ ነው በማለት በዘመንና በጊዜ የተፈታው አዝማሪ ከራሱ አፍልቆ ፣ የህዝቡን ስነ ልቡናና የሹክሹክታ ድምጽ ሰምቶ በአጭር አገላለፅ ለመተቸት ወይም ለማሞገስ ያበረከተው አስተዋጿ ከፍተኛ ነው ብለዋል ፡፡

መርሀ ግብሩ እስከ ግንቦት 16 የሚቀጥል ሲሆን ቅኔና የአዝማሪ ጨዋታን ጨምሮ 16 የሚሆኑ ጥናታዊ ፅሁፎች ይቀርቡበታል፡፡