የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል

በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ምክንያት ትምህርታቸውን አቋርጠው የነበሩ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደረገላቸው

በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ለመማር ምቹ ባልሆኑ የጦርነት ቀጠና ውስጥ በነበሩ የተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በትምህርት ገበታቸው ላይ የነበሩ እና ትምህርታቸው ለአንድ ዓመት ያህል አቋርጠው በትምህርት ሚኒስቴር ባደረገው ዳግም ምደባ ወደ ዩኒቨርስቲያችን ለመጡ ተማሪዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ተደረገላቸው፡፡

በስነ ስርዓቱ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች ዲን ዶ/ር ምኒችል ግታው ለተማሪዎቹ እንደተለፁት የቆያችሁበት ሁኔታ ፈተናው የናንተ ብቻ ሳይሆን የኛም፤ የሀገሪቱም ፈተና ነው ብለዋል፡፡ በዚህ ችግር ውስጥም ጥንካሬ እንማራለን፣ ለሌሎችም ማሰብን ትምህርት በመውሰድ መልካም ጎንኑ ለመመልከት በመሞከር ትምህርት መውሰድ ይቻላል ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ትኩረት አድርጎ ከሚሰራባቸው አንዱ ተከባብሮ፣ ተዋዶ በመኖር ላይ የተመሰረተ በመሆኑ ስክነት እና ብስለት ለሀገር እና ህዝብ አንድነት የሚኖራቸውን ጉልህ ሚና በእያንዳንዳችሁ ውስጥ እንዲኖር እንፈልጋለን ብለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ አስተዳደር ጉዳዮች ም/ፕሬዝዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ በበኩላቸው በትምህርት ሚኒስቴር በሀገሪቱ ተማሪዎች ዙሪያ የተሟላ መረጃ ስላልነበረ በዩኒቨርስቲያችን አንድ ሳምንትም ሆነ ከዛም በላይ ችግር ለገጠማቸው፤ ነባራዊውን ሁኔታ በመገንዘብ ላሳዩት ትዕግስት አመስግነዋል፡፡ ይህም ችግር ለቀጣይ እንዳይፈጠር ትምህርት ሚኒስቴር ወደፊት የሁሉንም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በመረጃ ቋት እንደሚያስቀምጥ ተስፋቸውን ገልፀዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ አያይዘውም የተማሪ ዓላማ ተምሮ ለደረጃ መብቃት ነው፡፡ ስለዚህ ከዋና ዓላማችሁ ውጭ ስትሰማሩ እራስንም ሀገርንም ዋጋ የሚያስከፍል በመሆኑ ዓላማችሁን መሳት የለባችሁም፤ ዩኒቨርሲቲ ካወቃችሁበት ሰው የምትሆኑበት ካለወቃችሁበት ሰውነታችሁን የምታጡበት ነው ብለዋል፡፡

በዕለቱ የሬጅስትራርና አልሙናይ ማኔጅመንት ዳይሬክቶሬት ዶ/ር ብርሌው እና የስነ-ልቦና ማማከር የስራ ክፍል ባልደረባ ዶ/ር አብዮት ለተማሪዎች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በመርሃ ግብሩም በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢንፎርሜሽንና ስትራቴጅክ ኮሙኒኬሽን ም/ፕሬዝዳንት ስር የባህል ማዕከል የተለያዩ አስተማሪና አዝናኝ የሆኑ ጥዕመ ዜማዎችንና ግጥሞችን አቅርበዋል፡፡