የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ሞጁል

የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ ሞጁል ላይ አውደጥናት ተካሄደ

*****************************************************************************************************የትምህርት ሚንስቴር ከኢትዮጵያ ታሪክ ባለሙያዎች ማህበር ጋር በመተባበር የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ በሚል ርዕስ የተዘጋጀውን ሞጁሉ  ለአንደኛ ዓመት የዩኒቨርሲቲ  ተማሪዎች  በሦስት ክሬዲት አወር በኮመን ኮርስ ለመስጠት  የሚያስችለውን  የግንዛቤ ማስጨበጫ አውደጥናት በርካታ የታሪክ ሙሁራን በተገኙበት  በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ ሕንፃ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተከታታይና  ርቀት ትምህርት ፕሮግራም ዳይሬክተር ዶ/ር አበበ ድረስ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከ11 ዓመት በፊት በ2004 ዓ.ም ከሃያ በላይ የሚሆኑ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህራንን በመጋበዝ ለዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደ ኮመን ኮርስ እንዲሰጥ የውይይቱ ዋና አጀንዳ እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ወጣቶችን እና ማህበረሰቡን ማንቃት በታሪክ በኩል ያለውን ክፍተት ለመሙላት የታሪክ ትምህርትን በኮመን ኮርስ እንዲሰጥ እና የታሪክ ሙሁራን ማህበር  መመስረት እንደነበረ ጠቅሰው ከ11ዓመት በኋላ ተሳክቶ በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ እንደ ዶ/ር አበበ ገለፃ ማህበሩ መመስረቱ እና ትምህርቱን በኮመን ኮርስ መሰጠቱ ጥሩ ነገር ሆኖ ቀጣይ ትግበራው ላይ ሊገጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ሙሁራዊ በሆነ መንገድ ለመፍታት የእለቱ የውይይት መድረክ ሚናው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ታዬ ደምሴ የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ዲን በበኩላቸው የታሪክ ትምህርት እንደ ኮመን ኮርስ ሲሰጥ ስድስተኛው ኮርስ መሆኑን ጠቅሰው ኮርሱ ለተማሪዎች በትክክል እና በአግባቡ ተደራሽ እንዲሆን የመምህራን ድርሻ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ትምህርቱን በሀገር አቀፍ ደረጃ  በኮመን ኮርስ ለመስጠት ረጅም አመታት መውሰዱን እና በጉዳዩ ላይም ብዙ ክርክር እና እሰጣገባ እንደነበረ ጠቅሰው በታሪክ ሙሁራን ማህበር ብርቱ ትግል ለውጤት መብቃቱን በመግለፅ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በጉዳዩ ዙሪያ ያበረከተው አስተዋፃ ከፍተኛ መሆኑን ዶ/ር ታዬ ተናግረዋል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የታሪክ መምህር እና ተመራማሪ የሆኑት ፕ/ር ሹመት ሲሻኝ አጠቃላይ የሞጁሉን አሰጣጥ እና አቀራረቡን በተመለከተ የመነሻ ጥናታዊ ፁሁፍ አቅርበዋል፡፡  የኢትዮጵያ ታሪክ እንደግዴታ ሆኖ ለሁሉም ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች አለመሰጠቱ ሀገራዊ ጉዳት ብቻ ሳይሆን ሙያዊ ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑን በጥናታዊ ፁሁፋቸው አመላክተዋል፡፡ እንደ ፕ/ር ሹመት ገለፃ ያለታሪክ አንድን ሀገር አንድ አድርጎ ማቆየት አስቸጋሪ መሆኑን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ የተለያየ ቋንቋ እና ባህል ያለው ህዝብ የዜግነት እና የጋራ ስሜት ሊያዳብር የሚችለው የሀገሪቱን ታሪክ በማስተማር እና በማሳወቅ የጋራ ማድረግ ሲቻል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመጨረሻም በምክክር መድረኩ ተሳታፊ መምህራን በኩል የታሪክ ትምህርት ላለፉት 30 ዓመታት በተዳከመበት እና ቀድሞ የነበረው ትምህርት ክፍሎች በተወሰነ ደረጃ ትኩረት አጥተው  እና መምህራንም ሌላ የትምህርት መስክ ቀይረው ባለበት ሁኔታ ትውልዱን ወደራሱ ታሪክ እንዲመለስ ለማድረግ ጠንከር ያለ አካሄድ እና የክትትል ስራ እንደሚያስፈልግ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ታሪክ  (History of Ethiopia and the Horn) የሚል ርዕስ ያለው ሞጁሉ በሰባት ምዕራፎች የተከፋፈለና 187 ገጾች የያዘ ሲሆን በአንድ ሴሚስተር ለማዳረስ ከተሰጠው ሰዓት አንፃር ከባድ በመሆኑ ማብሪሪያ እንዲሰጣቸው ጠይቀው ከመድረክ ማብራሪያ እና ገለፃ ተሰጥቶበታል ፡፡