የአድዋ ድል

አድዋ ኢትዮጵያዊያንን ብቻ ሳይሆን መላውን ጥቁር ህዝቦች የነፃነት ድል ያጎናጸፈ ነው” ዶ/ር ፍሬዉ ተገኘ

የካቲት 23 ቀን 2014ዓ.ም (ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ)

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬዉ ተገኘ እንደገለጹት የአድዋ ድል ሲነሳ የማንረሳቸዉ ሁለት ሰዎች አሉ፡- እነሱም እምዬ ሚኒሊክና እቴጌ ጣይቱን አለማንሳት አይቻልም ብለዋል፡፡ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ለሚኒሊክ የሚሰጡትን ቦታ ያክል እኛ ኢትዮጵያውያን እየሰጠነዉ ስላልሆነ ይህ መታሰብ እንዳለበት ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡ አድዋ የኢትዮጵያውያንን ጀግንነትና ድል አድራጊነት በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ እንዲታወቅ ያደረገ የድል ታሪክ መሆኑንም ዶ/ር ፍሬዉ ገልጸዋል።

የአሁኑ ትውልድም አባቶቻችን ከጠላት ጋር ተናንቀው ነፃ ሀገር እንዳስረከቡን አውቆ ኢትዮጵያን በአንድነት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማቆየት እንዳለበት አመልክተዋል። ዶ/ር ፍሬዉ አክለዉም የነፃነት ትግሉ አሁንም የሚቀጥል ነው፤አድዋን ዘክረነዉ ብቻ የሚያልፍ ሳይሆን ወደፊትም መልዕክት ይዘን የምንታገልበት ነው ብለዋል፡

የዩኒቨርሲቲው የታሪክ ምሁራንም በዓሉን የተመለከቱ ጥናታዊ ፅሁፎች ያቀረቡ ሲሆን ዶ/ር ገረመዉ እስከዚያ “የአድዋ ጦርነት” በሚል ርዕስ የጦርነቱን መነሻ ምክንያት፣ የጦርነቱን ደረጃዎችና በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችን የቀደምት ታሪክ ጻህፍትን ስራዎች በማጣቀስ አቅርበዋል፡፡

ዶ/ር ገረመዉ የጦረነቱን መነሻ ሲያቀርቡ የአጤ ምኒልክ እና የኢጣሊያ ግንኙነት የተጀመረው ቀደም ባሉት ጊዜያት ቢሆንም በተለይ የአድዋ ጦርነት ፔትሮ አንቶኒሊ የሚባል ኢጣሊያዊ ከፈጠረዉ የዲፕሎማሲ ተንኮል ጋር ይያያዛል ብለዋል፡፡ በጦርነቱ የደረሱ ጉዳቶችም በርካታ እንደነበሩ ገልፀው በአድዋ ጦርነት 7,000 አካባቢ የጠላት ወታደሮች ሲገደሉ 1,428 ቆስለዋል፤ 3,000 የጦር ምርኮኛ ሆነዋል፡፡ በአንፃሩ በኢትዮጵያ በኩል ከ4,000—6,000 የሚደርሱ ተዋጊዎች በጀግንነት ሲሰው 8,000 ደግሞ መቁሰላቸውን ባቀረቡት ጥናታዊ ጽሁፍ አብራርተዋል፡፡

ሌላው የፅሁፍ አቅራቢ አቶ ሰሎሞን አሻግሬ በበኩላቸዉ “ከአድዋ የምንወስዳቸው ትምህርቶች” በሚል ርዕስ በጦርነቱ ወቅት የነበረውን ጀግንነት፣ርህራሄ፣ህዝባዊ ተሳትፎ፣ጥንቃቄ እና ሀገራዊ የፖለቲካ አንድነት በማንሳት ለተሳታፊዎች በወቅቱ የነበረዉን ሁኔታ አስገንዝበዋል፡፡ ተሳታፊዎችም በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ሰፋ ያለ ጥያቄና አስተያየት ያቀረቡ ሲሆን ከመድረኩ ምላሽ እና ማብራሪያ ተሰጥቶባቸዋል፡፡

በበዓሉ መነባንብ፣ ግጥም፣ አጭር ተውኔት እና በአማራ ፖሊስ ማርች ባንድ የቀረቡ ጥዑመ  ዜማዎች ለበዓሉ ድምቀት ከፍተኛ ሚና ነበራቸው፡፡

 126ኛው የአድዋ ድል በዓል የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንትና ከፍተኛ አመራሮች፣ የዩኒቨርሲቲው ሰራተኞች፣ጥሪ የተደረገላቸዉ እንግዶች እና የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በተገኙበት የካቲት 23/2014 ዓ.ም በዩኒቨርሲቲዉ ጥበብ ህንጻ የመሰብሰቢያ አዳራሽ ተከብሯል፡፡

   

ዘጋቢ፦ ሸጋዉ መስፍን

 
 
 
 
 
ReplyForward