የችግኝ ተከላ ፕሮግራም በቤዛዊት ተራራ፣ ባሕር ዳር

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በቤዛዊት ተራራ ላይ የችግኝ ተከላ ፕሮግራም አካሄደ

(ሐምሌ 04/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-BDU) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ቢሮ የዩኒቨርሲቲውን መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች በማስተባበር ከሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም ኤንድ ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ማኅበር ጋር በመተባበር ቤዛዊት ተራራ ላይ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር አካሄዱ፡፡

በችግኝ ተከላው ላይ ተግኝተው ሲያስተባብሩ ያገኘናቸው የሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም ኤንድ ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ  ትዝታ የኔዓለም ማኅበሩ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በየዓመቱ የችግኝ ተካላ እንደሚያካሂድ ተናግረው በእለቱ ከዩኒቨርሲቲው ጋር  በመሆን  በቤዛዊት ተራራ  ላይ ተንሰራፍቶ የነበረውን መጤ አረም (ላንታና ካማራን) በማፅዳት በማሕበሩ የችግኝ ጣቢያዎች የለሙ ሐገር በቀል ዛፎችን  መትከላቸውን ተናግረዋል፡፡

ስራ አስኪያጇ አክለውም ተራራውን በአገር በቀል ችግኝ ለማልማት በርካታ ችግኞች በችግኝ ጣቢያቸው እንዳሉና ቀደም ሲል  በመጤ አረም (ላንታና) የተወረረውን የተራራውን ክፍል የማፅዳት ስራ መሰራቱን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ግን መጤ አረሙን ለማስወገድ በየጊዜው ክትትል የሚፈልግ ስራ በመሆኑ ወጥና ቀጣይነት ያለው የተፈጥሮ ሐብት ስራን ለመስራት እና በየዓመቱ የሚተከሉ ችግኞች ከሰው እና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ በማድረግ እና ውሃ በማጠጣት፤ በመኮትኮት ችግኞችን የሚንከባከቡ በርካታ የሰው ሃይል በመቅጠር ዘላቂነት ያለው የተፈጥሮ ሐብት ስራ እየተሰራ  መሆኑን ስራ አስኪያጇ ተናግረዋል፡፡

የችግኝ ተከላው ፕሮግራም አስተባባሪና የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ተቀዳሚ ዳይሬክተር ዶ/ር ተሰማ አይናለም  በበኩላቸው  የችግኝ ተከላ ፕሮግራሙ ዩኒቨርሲቲው እንደሃገር የአረንጓዴ አሻራ (Green legacy) ተብሎ ከመነገሩ በፊት ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በይልማና ዴንሳ፣ ቋሪት እና ሰከላ ወረዳዎች  አዋሳኝ በሆነው ብር አዳማ አካባቢ እና በመራይ  እንዲሁም በቤዛዊት ተራራ ላይ እየተሰራ ያለ የተፈጥሮ ሐብት ስራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ዳይሬክተሩ አክለውም በ2014 ዓ.ም ዓመቱን ሙሉ ሲለሙ የቆዩ የተለያዩ ሀገር በቀል ችግኞችን በቅርቡ የብር ዓዳማ ተራራን ጨምሮ በሌሎች ቦታዎችን ላይ የመትከል መርሃ ግብር እንደሚካሄድ አክለው ተናግረዋል፡፡ የቤዛዊት ተራራ  አካባቢው ድንጋያማ በመሆኑ ለአካባቢው ተስማሚ የሆኑ የግራቢያ ችግኞችን ከሶሳይቲ ኢኮ-ቱሪዝም ከተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በመተባበር ችግኞች እንደተተከሉ ገልፀዋል፡፡

በችግኝ ተካላ መርሃ ግብሩ ላይ ከሁሉም ግቢዎች የተወጣጡ መምህራን እና የአስተዳደር ሰራተኞች ተሳትፈዋል፡፡