የተማሪዎች ምረቃ ስነ-ስርአት

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በተለያዩ መርሃ ግብሮች ያሰለጠናቸውን ተማሪዎች በድምቀት አስመረቀ
=============================================
[ነሐሴ 21/2014 ዓ/ም፤ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ -ባዳዩ] የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ፣ በሁለተኛ ፣በሦስተኛ ድግሪ፣ በPGDT፣ በHDP እና በማሪታይም ፕሮግራም ትምህርታቸውን ሲከታተሉ የቆዩ 4ሺህ 616 ወንድ እና 1ሺህ 900 ሴት በድምሩ 6 ሺህ 515 ተማሪዎችን ዛሬ ነሃሴ 21 /2014 ዓ.ም በድምቀት አስመረቀ፡፡
 
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ለ60ኛ ዓመት ያበቃው እና ዩኒቨርሲቲውን ከመሰረቱት ሁለት የትምህርት ተቋማት አንዱ የሆነው የቀድሞው ፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት የአሁኑ የባሕር ዳር ቴክኖሎጂ ተቋም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአራቱ የምህንድስና መርሐ-ግብሮች በኬሚካል፣ በሲቪል፣ በኤሌክትሪካልና በሜካኒካል ምህንድስና ዘርፎች ዕውቅና ለመሰጠት የመጀመሪያውን ዙር ማጣሪያ አልፎ ሁለተኛውን እና የመጨረሻውን ዙር በመጠባበቅ ላይ ይገኛል ሲሉ ተናግረዋል፡፡ ውጤቱ ዩኒቨርሲቲውን ከሰሃራ በታች ከሚገኙ ሀገራት የመጀመሪያው እንደሚያደርገውም ገልፀዋል፡፡ ፕሬዚዳንቱ አክለውም ከፖሊ ቴክኒክ ኢንስቲትዩት አድጎ የወጣው የኢትዮጵያ ቴክስታይልና ፋሽን ቴክኖሎጂ ኢንስቲትዩት በያዝነው ዓመት 15 መመዘኛዎችን አልፎ ሁለት ቤተ-ሙከራዎችን ዕውቅና በማሰጠት የማስተማሪያ ፋብሪካ ፅንሰ ሐሳብን ተግባር ላይ ማዋሉን ገልፀው ተቋሙ የሰራው ጠንካራ ስራ በሀገሪቱ ብሎም በምሥራቅ አፍሪካ ቀዳሚ እንደሚያደርገው በመግለፅ ለዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
 
በተማሪዎች የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ የተገኙት የዕለቱ የክብር እንግዳና በኢትዮጵያ፣ በጅቡቲና በአፍሪካ ኅብረት የኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ ባስኑር ለዕለቱ ተመራቂ ተማሪዎች በመልዕክታቸው “ የዛሬ ተመራቂዎች ምንም እንኳን ከቤተሰቦቻችሁ ብትወጡም የቤተሰቦቻችሁ ብቻ አይደላችሁም፤ የመላው ኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻም አይደላችሁም፤ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጭምር ሃብት ናችሁ ሲሉ ተናግረዋል ”፡፡ ኢንዶኔዝያ እና ኢትዮጵያ ሁሉን አቀፍ ትብብር እያደረጉ ከ60 ዓመት በላይ መቆየታቸውን ተናግረው በትምህርት ዘርፍ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር እየሰሯቸው ያሉ የሁለትዮሽ የትብብር ስራዎች ጉልህ ማሳያ መኾናቸውን አምባሳደሩ ጠቁመዋል ፡፡ ትምህርት የሁሉ ነገር መፍቻ ቁልፍ ነው ያሉት አምባሳደሩ የዛሬ ተመራቂ ተማሪዎችን እንኳን ደስ ያላችሁ ብለዋል፡፡
 
ዩኒቨርሲቲው ባሳለፍነው ዓመት ለሀገራችን ኢትዮጵያ በማህበረሰብ አገልግሎት ጉልህ አስተዋፆ ላበረከቱት ለብፁዕ አቡነ ኤርምያስ፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሰሜን ወሎ እና በአማራ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት የኦሮሚያ ልዩ ዞን ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስ እና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል፤ እንዲሁም በስፖርቱ ዘርፍ በጎ ስራ ለሰራችው ለኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የክብር ዶክትሬት ማዕረግ የሰጠ ሲሆን ከኢንዶኔዥያ አምባሳደር አል ቡሲራ እና ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ እጅ ተቀብለዋል፡፡
 
ብጹዕ አቡነ ኤርምያስ ለሀዋሪያዊ ተልኮ ከሀገር ውጭ ቢሆኑም ካሉበት ሀገር ኾነው ባስተላለፉት የቪዲዮ መልዕክት የተሰጠው የክብር ዶክትሬት ለእኔ ሳይሆን በጸሎት ሲጠብቁኝ ለነበሩት ለብጹዕ አቡነ ቄርሎስ፣ ከጎኔ ኾነው በምክር ለረዱኝ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ለሚፋጠኑት ካህናት፣ ዲያቆናት፣ ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር ድልድይ ኾነው ላገናኙኝ የመስጊድ ኮሚቴ አባላት፣ ሰብዓዊ ግዴታቸውን ለተወጡ አባቶቻችን እና እናቶቻችን ነው ሲሉ ተናግረዋል።
 
አልተማሩም ያልናቸው ወገኖቻችን በመስዋእትነት ያቆዯትን ሀገራችንን ተማርን ያሉ ሰዎች በየቀኑ የመለያየት፣ የማፍረስ ፈጠራ እየፈጠሩ ወገንን ከወገን ሲለያዩ፣ የተገነባውን ሲያፈርሱ እየተመለከትን ነው ብለዋል። የጥፋት ተቃራኒ የሆነውን ልማት እንድታለሙ፣ ራሳችሁን ረድታችሁ ሀገራችሁን እንድትረዱ፣ አንድ የሆነችው ሀገራችሁና ሕዝባችሁ በአንድነቱ እንዲቀጥል አደራ ሲሉ በአፅንዖት ተናግረዋል።
 
በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የክብር ዶክተር ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተሰጣት የክብር ዶክትሬት ለእሷ ብቻ ሳይኾን በአትሌቲክሱ ዘርፉ ኢትዮጵያን በዓለም አቀፉ አደባባይ ስሟን ለሚያስጠሩ አትሌቶችና አሰልጣኞች እንዲሁም ለአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ከፍተኛ ሞራልና መነሳሳትን ይፈጥራል ስትል ተናግራለች ፡፡ የክብር ዶክተር ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ተመራቂዎች በዩኒቨርሲቲ የቀሰሙትን እውቀት ተጠቅመው ሀገራቸውን በቅንነትና በታማኝነት እንዲያገለግሉ ስትል መልዕክት አስተላልፋለች ፡፡
 
በ2014 ዓ.ም የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ በትምህርታቸው አብላጫ ውጤት ላስመዘገቡ እና ከሁሉም ግቢ ለተውጣጡ ተማሪዎች የምስክር ወረቀት፣ የሜዳሊያ እና የዋንጫ ሽልማታቸውን ከዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት እና ከአካዳሚክ ጉዳዩች ም/ፕሬዚዳንት እጅ ተቀብለዋል፡፡
 
በመጨረሻም በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የስራ አመራር ቦርድ አባላት፣ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር የሺመብራት መርሻ፣ ፕሮፌሰር ማስረሻ ፈጠነ የBiT እና EiTEX አማካሪ ቦርድ የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ም/ከንቲባና የዩኒቨርሲቲው ቦርድ አባል ዶ/ር ድረስ ሳህሉ እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡
 
ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ- ባዳዩ-BDU
ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ
Wisdom at the source of Blue Nile
Thank you for visiting, inviting and sharing our Pages!
Thank you for your likes and comments!
ለተጨማሪመረጃዎች፡-
Telegram ፡- t.me/BDU_ISC_Official
website :- www.bdu.edu.et