የባሕር ዳር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ከተማ ርክክብ

የባሕር ዳር ከተማን መዋቅራዊ ፕላን ከተማ አስተዳደሩ ተረከበ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመተባበር የባሕር ዳር ከተማን የሚያዘምን መዋቅራዊ ፕላን ሰርቶ ለከተማ አስተዳደሩ አስረክቧል፡፡

 

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በርክክብ ስነስርዓቱ  እንደገለጹት የባሕር ዳር ከተማን መዋቅራዊ ፕላን በዘመናዊ መልኩ ለመስራት ዩኒቨርሲቲው ጽ/ቤት አቋቁሞ የተለያየ ሙያ ያላቸውን ሙያተኞች በማሳተፍ ለሌሎች ከተሞች ተሞክሮ የሚሆን ፕላን በመስራት ማስረከብ መቻሉ አኩሪ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ፕሬዘዳንቱ አክለውም ፕላኑን ለመስራት ከአንድ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ይፈጅ የነበረውን በ20 ሚሊዮን ብር በማህበረሰብ አገልግሎት ስም ሰርቶ ማስረከቡ ይበል የሚያስብል ተግባር መሆኑን ገልፀው ባሕር ዳር ከተማ የክልል ዋና መዲና እንደመሆኗ መጠን ውብና ማራኪ ብትሆንም  በተለየ መልኩ ደምቃ የምትታይ ከተማ ለማድረግ ፕላኑ መዘጋጀቱን አንስተዋል፡፡ ከተማ አስተዳደሩም  መሪነቱን በመውሰድ በምናብ ውብ ሆና የምትታየውን ከተማ እውን ለማድረግ በቅንጅትና በፍጥነት  ሁሉን  ባሳተፈ ርብርብ ወደ ትግበራው መግባት ቀዳሚው ተግባር መሆኑን በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

 

የባሕር ዳር ከተማ ተቀዳሚ ከንቲባ ክቡር ዶ/ር ድረስ ሳህሉ አንድ ከተማ ተውባና ማራኪ ሆና እንድትታይ ከሚያደርጓት ነገሮች አንዱና ዋናው ደረጃውን የጠበቀ መዋቅራዊ ፕላን ስለሆነና ይህን ስራ በኃላፊነት ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ወስዶ መስራቱ እጅግ በጣም  የሚያስመሰግን መሆኑን ተናግረዋል፡፡

 

ዶ/ር ድረስ በማስከተል ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና ባሕር ዳር ከተማ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገፅታዎች መሆናቸውን አውስተው ዩኒቨርሲቲው የምሁራን መንደር በመሆኑ ይህንን መዋቅራዊ ፕላን  ጊዜ በመውሰድ በርካታ ሙያተኞችን፣የአገር ሽማግሌዎችንና የሚመለከታቸውን የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተደጋጋሚ መድረክ ምክረ-ሃሳብ በመቀበል መስራቱ አኩሪ ተግባር መሆኑን በአንክሮ ገልፀዋል፡፡

 

በመርሃ ግብሩ ላይ መዋቅራዊ ፕላኑን በተመለከተ የኢንፎርሜሽንና ስትራቴጂክ ኮሚኒኬሽን ጽ/ቤት ከባሕር ዳር ከተማ መዋቅራዊ ፕላን ፕሮጀክት ጽ/ቤት ጋር በጋራ ያዘጋጁት ተንቀሳቃሽ ምስል ለታዳሚዎች ቀርቧል፣ በፕሮጀክቱ አባላት የተለያዩ ይዘት ያላቸው የፅሁፍና የምስል ገለፃ ቀርቧል፣ በቀረቡት ፅሁፎች ዙሪያ በዶ/ር ፍሬው፣በዶ/ር ድረስ እና የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር በሆኑት ዶ/ር መንግስቴ አባተ መሪነት ውይይቱ ተካሂዶ ታዳሚዎች የተሰራው ፕላን እንደ አስደሰታቸውና በቅርብ ወደ ትግበራው መግባት ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡