የሥርዓተ-ፆታ እና ልማት ጥናቶች አገር አቀፍ ጉባኤ

የሥርዓተ-ፆታ እና ልማት ጥናቶች ትምህርት ክፍል  እያካሄደ የነበረው አገር አቀፍ ጉባኤ ተጠናቀቀ

 

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ፋኩልቲ ስር የሚገኘው የሥርዓተ-ፆታ እና ልማት ጥናቶች ትምህርት ክፍል ከ "Friedrich Ebert Stiftung"  ጋር በመተባበር  "National conference on Contemporary Gender Issue" በሚል መሪ ቃል ሁለተኛውን አገር አቀፍ 

ጉባኤ በባሕር ዳር ከተማ ከሚያዚያ 05-06/2014 ዓ.ም ለሁለት ተከታታይ ቀናት ተካሄዶ  ተጠናቀቀ፡፡

የፋኩልቲው ዲን ዶ/ር ታዬ ደምሴ ለፕሮግራሙ መሳካት ጉልህ አስተዋፅኦ ላበረከቱት አካላት ምስጋናና ለታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ጉባኤው አገር አቀፍ መሆኑ ለትምህርት ክፍሉ መጠናከር ያለው ፋይዳ የላቀ መሆኑንና ትምህርት ክፍሉም ከመጀመሪያ ዲግሪ እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

 

መርሃ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዮች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ በኢትዮጵያ ካሉት ዩኒቨርሲቲዎች የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዘዳንት ሆነው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲን ያገለገሉት  ክብርት  አምባሳደር  ዶ/ር  የሽመብራት  መርሻን  ጨምሮ  ለመላው  ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዶ/ር እሰይ አክለውም የጉባኤው መካሄድ ትምህርት ክፍሉን አንድ እርምጃ ከፍ እንደሚያደርገውና ለወደፊት ተጠናክሮ እንዲቀጥል ከሚቀርቡት ጥናቶች በመነሳት የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ እንደሚለይ ተናግረዋል፡፡

የክብር እንግዳዋ ክብርት  አምባሳደር ዶ/ር  የሽመብራት መርሻ  ይህን ጉባኤ  ለመታደም  ከሩቅም ከቅርብም ለመጡ ተሳታፊዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ቤታቸውም ቤተሰባቸውም መሆኑን አውስተዋል፡፡ በማስከተል ከአሁን  በፊት ዩኒቨርሲቲውን በማገልገል ላይ እያሉ ት/ት ክፍሉን ለማቋቋም በርካታ ውጣ ውረዶችን  እንዳሳለፉና በተለይ በአውሮፓ አገራት ያለውን የስርዓተ ፆታ የተራራቀ ልዩነት ተገንዝበው በአገራችንም የሴቶች ተሳትፎ ጎልቶ እንዲወጣ የዘወትር ህልማቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አምባሳደሯ በማስከተል  በአገራችን "ስርዓተ-ፆታ"  ሲባል የሴቶች  ጉዳይ ብቻ አድርጉ  የማየት  የተሳሳተ አስተሳሰብ እንዳለና ዛሬ ላይ ያ አስተሳሰብ ተሰብሮ የሁሉም አጀንዳ መሆኑን የሚያመላክተው  ይህ ደማቅ ጉባኤው መካሄዱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ጉባኤውም ት/ት ክፍሉ ከመዳህ ዘሎ  በእግሩ መቆሙን ማሳያና የሴቶችን ተሳትፎ ከፍ ለማድረግ  የማንቂያ ደወል እንደሆነ ዶ/ር የሽመብራት በደስታ ገልፀዋል፡፡

የእለቱን ቁልፍ መልዕክት ያስተላለፉት የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ ም/ኃላፊ ወ/ሮ ሰላም አለማየሁ በአገራችን ብሎም በክልላችን ሴቶች በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካው መስክ ያላቸው ተሳትፎና ውክልና አናሳ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ሰላም አክለውም ይህ የተሳትፎ ውስንነት ሴቶች የሚጠበቅባቸውን አስተዋፅኦ እንዳያበረክቱና ከድህነት አረንቋ እንዳይወጡ ቢያደርጋቸውም   ጭቆናውን ተቋቁመው  በሁሉም መስኮች ሴቶች እያስመዘገቡት ያሉት ቱርፋቶች በቀላሉ የማይታዩ መሆናቸውን አስገንዝበዋል፡፡

ምክትል ቢሮ ኃላፊዋ በማስከተል የስርዓተ-ፆታ እኩልነትን ለማረጋገጥ እየተሰሩ ያሉ አበረታች ተግባራት ቢኖሩም የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት የተለያዩ መሰናክሎች እንዳሉና ከእንቅፋቶችም መካከል በሴቶች ላይ ያለው የተዛባ አመለካከት፣ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች፣ጾታዊ ጥቃት፣የሴቶች የስራ ጫና፣ ተቋማዊ ተግዳሮቶች፣ወቅታዊ፣ሃገራዊና ክልላዊ ፈተናዎች በዋነኛነት ተጠቃሽ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

 

በተጨማሪም የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት የሴቶች፣ ህፃናትና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ  ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ በመተባበር በርካታ አኩሪ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ገልፀው በአሁኑ ወቅት በክልላችን ብቸኛ የሆነውን የለውጥ መሪነት ለስርዓተ- ጾታ  ዕኩልነት  የስልጠና ማዕከል (Transformative Leadership For Gender Equality Training Center) በፈለገ ሕይወት ሪፈራል ሆስፒታል መዘጋጀቱን እንዲሁም በዩኒቨርሲቲው ሴኔት ፀድቆ የስልጠና ካሪኩለም ተዘጋጀቶለት በቅርቡ ስራ የሚጀምር መሆኑንና ዩኒቨርሲቲው ለሴቶች ተሳትፎ  ፈር ቀዳጅነት በመሆን በተለያዩ  ፕሮግራሞች  የትምህርት አድል  መፍጠሩን  ም/ቢሮ ኃላፊዋ ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ሰላም በመልዕክታቸው ማጠቃለያም የስርዓተ-ጾታ ጉዳይ የአንድ ጾታ ጉዳይ ብቻ አለመሆኑንና በአንድ ክንፍ መብረር አለመቻሉን ሁሉም ሊረዳው እንደሚገባ በአንክሮ ገልፀው እኩልነቱን ለማስረፅ ከቤተሰብ ጀምሮ ት/ት ቤቶችና የሐይማኖት ተቋማት፣ የመንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ እንዲሁም ምሁራን  ሰፊ ሚና መጫወት እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡ 

 

የጽሁፍ አቅራቢዎች አገር በቀል ምሁራን በመሆናቸው ሴቶቸን የማብቃት  ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበትና ወደ አመራሩም ሲመጡ ወንበሩን ብቻ መስጠት ሳይሆን  የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርቡ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡  

 

በሙሉጎጃም አንዱዓለም

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ

      ባዳዩ-BDU

💦💦💦💧💦💦💧💦💦💦

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

Wisdom at the source of Blue Nile

🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎🔎

Thank you for Inviting, liking, sharing & visiting BDU pages!

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Telegram ፡- t.me/BDU_ISC_Official

Main Website :- www.bdu.edu.et

Facebook: - https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube ፡- www.youtube.com/c/BduEduEt

LinkedIn ፡- www.linkedin.com/school/bahir-dar-university

Twitter: - https://twitter.com/bdueduet