የለሙ ቦታዎችንና የተተከሉ ችግኞች ተጎበኙ

የ‘ሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም ኤንድ ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ማኅበር የለሙ ቦታዎችንና የተተከሉ ችግኞችን በተለያየ የስራ ኃላፊነት ላይ ባሉ አመራሮች አስጎበኙ

ከባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የተመሰረተው የ‘ሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም ኤንድ ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን በጎ አድራጎት ማኅበር በቤዛዊት ተራራ ዙሪያ የለሙ ቦታዎችንና የተተከሉ ችግኞችን በዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ከከተማ አስተዳደሩ በመጡ የተለያዩ የስራ ኃላፊዎች በ10/10/14 ጉብኝት አካሄዱ፡፡

የሶሳይቲ ፎር ኢኮቱሪዝም ኤንድ ባዮዳይቨርሲቲ ኮንሰርቬሽን ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ትዝታ የኔዓለም ማኅበሩ በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከ4 ሺህ በላይ አባላት እንዳሉት ገልፀው ማህበሩ የቤዛዊት ተራራን ለማልማት አቅዶ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ስራ አስኪያጇ አክለውም ተራራው በአገር በቀል ችግኝ ለማልማት በርካታ ችግኞች በችግኝ ጣቢያቸው እንዳሉና በቅድሚያ በመጤ አረም (ላንታና) የተወረረውን የማፅዳት ስራ በሰፊው መከናወኑን አስገንዝበዋል፡፡

ሁሉም አመራር የተራራውን ሰፊ ቦታ ተዘዋውሮ ሲጎበኝ ከአሁን በፊት ተራራውን ለማልማት እንቅፋት የሆነውን መጤ አረም (ላንታና) ሙሉ በሙሉ ከተራራው ለማጥፋትና በጎርፍ ተጠርጎ የሚወሰደውን ለም አፈር ለማስቀረት ብሎም ውሃን አቁሮ ለማቆየት የሚያስችል የእርከን ስራ መሰራቱን ጉብኝቱን የመሩት አቶ ጌታነህ ምንይችል ተናግረዋል ፡፡

ከጉብኝቱ መልስ ሰፊ ውይይት ሲካሄድ ውይይቱን የመሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ም/ ፕሬዘዳንት ዶ/ር ተስፋዬ ሽፈረው፣የአ.መ.ል.ድ. ም/ስራ አስኪያጅና የማህበሩ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ደጀኔ ምንልኩ፣ የባሕር ዳር ከተማ የከቲባ ጽ/ቤት ኃላፊ ወ/ሮ አስራት ሙጨ፣ የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ግብርናና  መሬት  መምሪያ  ኃላፊ  አቶ ትልቅሰው  እንባቆም እና ከአካባቢጥበቃ ባለስልጣን አቶ በልስቲ ፈጠነ ሲሆኑ በተደረገው ጉብኝት የታየውና ተራራውን ለማልማት በቅድሚያ መጤ አረሙን (ላንታናን) የማስወገድ ስራ በሰፊው መሰራቱ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑ ተገልጿል፡፡

አቶ ደጀኔ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለማህበሩ ለሚያደርገውን ያላሰለሰ ድጋፍና ክትትል ምስጋና አቅርበው ሌሌችም ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተራራውን ለማልማት ተቀናጅቶ በመስራት ከፅንሰ ሃሳብ የዘለለ ተግባር ተኮር ስራ ማከናወንና ተራራውን ከስጋት ቀጠና አላቆ የቱሪስት መስብ ማድረግ ተገቢ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አቶ ደጀኔ አክለውም ቦታው ትኩረት የሚሻው መሆኑን አስገንዝበው እንደዚህ ስናስታውሰው ብቻ ሳይሆን ሁሉም የሚመለከተው አካል ድርሻውን በመወጣት መጠነ ሰፊ ስራ ተሰርቶ ተራራው ደረጃውን የጠበቀ የቱሪስት መዳረሻ ሆኖ ማየት እንደሚሹ ገልፀዋል፡፡

ዶ/ር ተስፋዬ በበኩላቸው የአካባቢው ማህበረሰብ ያለምንም ስጋት የሚንቀሳቀስበት፣ የሚዝናነበትና ለከተማውም የገቢ ማስገኛ ሆኖ ቱሪስቶችን የሚስብ ስራ ለመስራት ሁሉም መረባረብ ስላለበት ከዩኒቨርሲቲ ውጭ ያሉ ተቋማትም በምርምር የተደገፈ ስራ በተራራው ላይ ሰርተው ጥሩ ውጤት ማስመዝገብ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡

ወ/ሮ አስራት ማህበሩ ተራራውን ለማልማት ስላደረገው አስተዋፅኦ ምስጋና አቅርበው ጉዳዩን የሁላችን አድርገን በመውሰድ ከማን ምን ይጠበቃል የሚለው ተለይቶ እንዲታወቅና ለወደፊት ሁሉም ትኩረት ሰጥቶ እንዲሰራ አስገንዝበዋል፡፡ በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት የአማራ ልዩ ኃይል ቤተመንግስቱን እንዲጠቀምበት ስለተደረገ በአካባቢው የነበረው ስጋት መወገዱን ጠቁመው ለማህበረሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እንዲሰራና ሁሉም ተረባርቦ ተራራው በማልማት የከተማውን ውበት መጨመር እንደሚቻል ወ/ሮ አስራት ተናግረዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ አመራሮች፣ጉዳዩ የሚመለከታቸው የከተማው ሴክተር መስሪያ ቤት ኃላፊዎችና የማህበሩ አባላት ሲሆኑ በተካሄደው ሰፊ ጉብኝትና ውይይት ማህበሩ የወደፊት የትኩረት አቅጣጫውን እንዲለይ መደረጉንና በቅርቡ በርካታ ችግኞች እንደሚተከሉ ተገልጿል፡፡

በሙሉጎጃም አንዱዓለም