የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ኃይል ልማት ስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ ጉብኝት

የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ኃይል ልማት ስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጉብኝት አካሄደ

**************************************************************

ጥር 30/2015 ዓ.ም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ) የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የሰው ኃይል ልማት ስራ ስምሪትና የቴክኖሎጂ ቋሚ ኮሚቴ የዩኒቨርሲቲውን የተለያዩ ግቢዎች ተዘዋውረው በማየታቸውና ተማሪዎችንም ጠይቀው ያገኙትን የምልከታ ውጤት በፕሬዘዳንት ጽ/ቤት የዩኒቨርሲቲውን ፕሬዜዳንት ጨምሮ ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት  ውይይት ተካሂዷል፡፡

የኮሚቴው ም/ሰብሳቢ ዶ/ር ቤተልሔም ላቀው እና የኮሚቴው አባልና የትምህርት ዘርፍ ኃላፊው አቶ ፍሬው ተስፋዬ መድረኩን በመምራት በተደረገው ውይይት ኮሚቴው ዩኒቨርሲቲው የአገር አለኝታ እንደሆነና ለማመን በሚያዳግት ደረጃ የምድረ ግቢ ውበት ስራ መከናወኑና ሌሎችንም በርካታ አኩሪ ተግባራት በምልከታቸው ያዩበት ፍሬአማ የስራ ጉብኝት ማካሄዳቸውን በአንክሮ ገልጸዋል፡፡   

ኮሚቴው ያቀረበው ሪፖርት አብዛኛው ለሌሎች መልካም ተሞክሮ የሚሆን ስራ በተለያዩ ግቢዎች ማየታቸውን የሚያወሳ ሲሆን አንዳንድ የሚታዩ ክፍተቶች ለምሳሌ የተሰሩት  ጥሩ ጥሩ ስራዎችን የማስተዋወቅ እና ተማሪዎችም በቆይታቸው የርዕስ በርዕስ ግንኙነታቸውን አጠናክረው ከዩኒቨርሲቲው ሲወጡ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነታቸውን እንዲያዳብሩ የሚያስችል ስራ ቢሰራ የሚል ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡  

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዘዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ የስራ ጉብኝት ያካሄደውን ኮሚቴ አመስግነው ዩኒቨርሲቲው ከመማር ማስተማሩ ባሻገር ዘርፈ ብዙ ተግባራትን እንደሚያከናውን ገልፀው ከዚህም በላይ ለመስራት እቅድ እንዳለውና በበጀት እጥረት ምክንያት ከታለመለት ግብ አለመድረሱን ተናግረዋል፡፡

ፕሬዘዳንቱ አክለውም ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ መሆን እንዳለባቸውና አስተዳደራዊ ነፃነት አግኝተው በትምህርቱም ሆነ በምርምሩ ዘርፍ በነፃነት ተንቀሳቅሶ በበጀት እጥረት ምክንያት ተጀምረው የቀሩ ግንባታዎችን በማስፈፀም ከዚህ በበለጠ ለሃገርና ለወገን የሚያግዝ ተግባር እንደሚያከናውንና የተሰሩትንም መልካም ተሞክሮዎች ለሌሎች ለማካፈል ፈቃደኛ መሆኑን እንዲሁም ዩኒቨርሲቲው 60ኛ ዓመቱን በማክበር ላይ ስለሆነ ተሞክሮዎችን ለማካፈል መልካም አጋጣሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ኮሚቴው ስለ ተማሪዎች የመውጫ ፈተናና ስለትምህርት ጥራት አንስቶ ውይይት ሲካሄድ የዩኒቨርሲቲው አካዳሚክ ጉዳዩች ም/ፕሬዘዳንት ዶ/ር እሰይ ከበደ የመውጫ ፈተና ዝግጅት መመሪያ ቀድሞ እየተሰራ መሆኑንና ተማሪዎችንም የማብቃት ስራ መሰራቱን እንዲሁም በመውጫ ፈተና ዙሪያ ከሁሉም ግቢ የተውጣጣ ግብረ ኃይል መቋቋሙን አስገንዝበዋል፡፡

የዩኒቨርሲቲው የአስተዳደር ጉዳዩች ም/ፕሬዘዳንት አቶ ብርሃኑ ገድፍ በበኩላቸው የተሰሩት መሰረተ ልማቶች እንዳሉ ሆነው ሌሎችንም ለመጨመር ዩኒቨርሲቲው ሰፊ ራዕይ እንዳለው አስገንዝበው በተለይ በህክምናና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ላይ እየታየ ያለው ለውጥና አገልግሎት ሰፊ ቢሆንም የውጭ አገር ሕክምናን እስከሚተካበት ደረጃ ማደግ ስለሚችል ከመንግስት ተገቢው ድጋፍና ክትትል ካለ በአገር በቀል እውቀት ለማህበረሰቡ መጠነ ሰፊ አገልግሎት መስጠት እንደሚቻል አሳስበዋል፡፡

አቶ ብርሃኑ በማስከተል ለዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ተግዳሮት የሆነው የበጀት እጥረት፣የግዥና የኦዲት ስርዓት ሲሆኑ አሁን ላይ ደግሞ ሊሰራ የታሰበው የዩኒቨርሲቲዎች መዋቅር ሁሉም ዩኒቨርሲቲ በተመሳሳይ መንገድ ሊሄድ ስለማይችል ሁሉም በስራው ልክ ይሰራለት ዘንድ ኮሚቴው የመፍትሄ አቅጣጫ እንዲያመጣ አሳስበዋል፡፡

ከተሰጡት የትኩረት አቅጣጫዎች መካከል ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ጉዳይ ኣሰሳቢ ስለሆነ በዚህ ዓመት አጠቃላይ በአገሪቱ ላሉ ዩኒቨርሲቲዎች 29 ሺህ ተማሪ ብቻ የመግቢያ ፈተናውን ስላለፉ በሌሎች ላይ የአዕምሮና የስነ ልቦናና ዝግጅት ላይ ሰፊ ስራ እንዲሰራ ኮሚቴው አሳስቧል፡፡

ከከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ`

Wisdom at the source of Blue Nile

Thank you for visiting and inviting our Pages!

Thank you for your likes, comments and shares!

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Facebook፡ https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube፡ https://www.youtube.com/@bduethiopia

Instagram፡www.instagram.com/bduethiopia

Tik Tok፡ https://www.tiktok.com/@bduethiopia

Telegram፡ https://t.me/bduethiopia

Twitter፡ https://twitter.com/bduethiopia

LinkedIn፡http://www.linkedin.com/school/bduethiopia

Website https://bdu.edu.et/

#BDU60th_ANNIVERSARY