ወጣት ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ፕሮጀክት

ወጣት ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀግብር ተካሄደ

--------------------------------------------------------------------------------------------------------

(ታህሳስ 07/2015 ዓ.ም ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-BDU) ከባሕር ዳር እስከ ደብረ ማርቆስ ባለው ኮሪደር ያሉ ወጣት ሴት ሥራ ፈጣሪዎች ላይ ትኩረት ያደረገ የፕሮጀክት ማስጀመሪያ መርሀ ግብር በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ጥበብ አዳራሽ ተካኬደ፡፡

በመድረኩ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ታፈረ መላኩ በአገራችን የወጣት የስራ አጥ ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሄዱን ገልፀዋል፡፡የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመማር ማስተማር ስራዎች ባሻገር ወጣቶች የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ የበኩላቸውን አስተዋጽዎ ማድረግ ይገባቸዋል ሲሉም አክለዋል፡፡

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ በበኩላቸው ዩኒቨርሲቲዎች ከምርምርና ማስተማር ስራዎች በተጨማሪ በየአካባቢው ያለውን ጸጋ ተጠቅመው ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲም አሜሪካን ሀገር ከሚገኘው Indiana ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር የስራ አጥ ወጣቶችን ችግር የሚያቃልል ስራ በጋራ እየሰራ እንደሆነ ገልጸው ለፕሮጀክቱ የገንዘብ ድጋፍ ላደረገው የአሜሪካ ኤምባሲ በኢትዮጵያ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ኃላፊ ዶ/ር ጌታሁን የማታ እንደገለጹት ፕሮጀክቱ ሦስት አላማዎች ያሉት ሲሆን አንደኛው የአጋር ዩኒቨርሲቲዎችን አቅም መገንባት፤ ሁለተኛው በኮሪደሩ ያሉ ስራአጥ የሆኑና የራሳቸው የቢዝነስ ሀሳብ ያላቸውን ወጣቶች በስልጠናና በገንዘብ በመደገፍ የራሳቸውን ስራ እንዲፈጥሩ ማድረግ፤ሦስኛው  በአገር ውስጥና በውጭ ሀገር ከሚገኙ ከተለያዩ ተቋማት ፤ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በተለይም አሜሪካ ከሚገኙ ተቋማት ጋር ትስስር መፍጠር ላይ መሰረት አድርጎ ላለፉት ሁለት አመታት ሲሰራ ቆይቷል ብለዋል፡፡

ባለፉት ሁለት አመታት በፕሮጀክቱ በሁለት ዙር ከ90 በላይ ስራ አጥ ወጣቶችን ማሰልጠን ተችሏል፡፡ ስልጠናውን ሲጨርሱም ባቀረቡት የቢዝነስ ሃሳብ ተወዳድረው የተሻለ የቢዝነስ ሃሳብ ላቀረቡ 12 ወጣት አሸናፊዎች የስራ ማስጀመሪያ የሚሆን ከ1.6 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ ሽልማት በጋራ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ወጣቶችም የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ገቢ እያገኙ በመስራት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ የነበረው ፕሮጀክት ውጤታማ በመሆኑም ዛሬ ላይ የተከፈተው አዲሱ ፕሮጀክት እንዲመጣ እድል ፈጥሯል፡፡ ሌላው በኢትዮጵያ ከሚገኙ 16 ዩኒቨርሲቲዎች የተውጣጡ ከፍተኛ አመራሮችን በማሰልጠን የአቅም ግንባታና የተለያዩ ስልጠናዎችን እንዲሁም በደብረ ማርቆስና በባሕር ዳር ያሉ የስራ ፈጠራ ልማትና ኢንኩቤሽን ማእከላትን በሰው ሀይልና በግብአት አሟልቶ የማደራጀት ስራ መሰራቱን አውስተዋል፡፡

የደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ኢንኩቤሽን ማእከል አስተባባሪ አቶ ይበልጣል ታረቀኝ እንደተናገሩት ፕሮጀክቱ ሕይወት የሚባል ሲሆን አላማውም ከቴክኒክና ሙያ፤ኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ተመርቀው ለወጡ ወጣት ሴቶች ስልጠና በመስጠት፤ የፈጠራ ስራና የቢዝነስ ሀሳብ ይዘው እንዲመጡ እገዛ በማድረግና በመደገፍ የራሳቸውን ድርጅት እንዲከፍቱ እራሳቸውን እንዲቀጥሩ ለማስቻል ነው፡፡

ፕሮጀክቱ ሦስት የስልጠና ማእከላት በባሕር ዳር፤በእንጅባራና በደብረ ማርቆስ ዩኒቨርሲቲዎች  ያሉት ሲሆን በእነዚህ ማእከላት የኢንተርፕርነር ስልጠናዎች ይሰጣሉ፡፡ ለስልጠና የሚያስፈልጉ  የስልጠና ሰነዶች ተዘጋጅተዋል ያሉ ሲሆን ለሦስቱም ዩኒቨርሲቲዎችና የዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ላደረጉት ድጋፍና ትብብር እንዲሁም ለአሜሪካ ኤምባሲ ምስጋና አቅርበዋል አቶ ይበልጣል፡፡

ቁልፍ መልእክት በማስተላለፍ መድረኩን ያጠቃለሉት የዓለም አቀፍ አጋርነት ለተቋማዊ ለውጥ እና አቅም ማጎልበት ምርምር እና ልማት ተባባሪ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ተሾመ ይዘንጋው ሲሆኑ በመድረኩ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ፤የደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲና የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው ተሳታፊዎች ተገኝተዋል፡፡

ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅም  በስልጠናው ያለፉ አካላት የስራ መፍጠሪያ ሀሳብና የመነሻ ገንዘብ ይኖራቸዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን አዲሱ ፕሮጀክትም የአንድ አመት ቆይታ እንደሚኖረው ተገልጿል፡፡

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ``

``Wisdom at the source of Blue Nile

Thank you for visiting and inviting our Pages!

Thank you for your likes, comments and shares!

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Facebook፡ https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube፡ https://www.youtube.com/@bduethiopia

Instagram፡www.instagram.com/bduethiopia

TikTok፡ https://www.tiktok.com/@bduethiopia

Telegram፡ https://t.me/bduethiopia

Twitter፡ https://twitter.com/bduethiopia

LinkedIn፡http://www.linkedin.com/school/bduethiopia

Website https://bdu.edu.et/

#BDU60th_ANNIVERSARY