ወደ የአማራ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ ዩኒቨርሲቲዉን ወክሎ የአማራ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ለሚሳተፈው ልዑካን ሽኝት አደረገ

የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ስፖርት አካዳሚ በስሩ አቅፎ ለያዛቸዉ 8 የሚሆኑ የተለያዩ የስፖርት ፕሮጀክት ሰልጣኞች መካከል አንዱ የሆነዉን ከ20 አመት በታች የእግር ኳስ ፕሮጀክት የአማራ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ላይ እንዲሳተፍ ወደ ከሚሴ ከተማ ሸኝቷል፡፡

 የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር ባህልና ስፖርት መምሪያ ባካሄደዉ የ2014 ዓ.ም የክለቦች ውድድር ላይ እንዲሳተፍ በማድረግ የዩኒቨርሲቲዉ የእግር ኳስ ክለብ ለዋንጫ ጨዋታ በማለፍ 2ኛ ደረጃን ይዞ በማጠናቀቅ የአማራ ክልል እግር ኳስ ፌዴሬሽን በሚያወዳድረዉ የአማራ ሊግ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ዩኒቨርሲቲዉን እና ከተማ አስተዳደሩን ወክሎ በከሚሴ ከተማ ከሀምሌ 02-21/2014 ዓ.ም ድረስ በሚካሄደዉ ክልል አቀፍ የክለቦች ውድድር ላይ ለመሳተፍ በመመረጣቸዉ ከሀምሌ 01/2014 ዓ.ም ጀምሮ ወደ ከሚሴ ከተማ አቅንቷል፡፡

 የዚህ ዉድድር ዋና አላማ ወደ አማራ ሊግ የሚገቡ ክለቦችን መለየት ሲሆን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ክለብ ዉጤታማ ሆኖ ወደ አማራ ሊግ እንዲገባ ለማስቻል መሆኑን የስፖርት አካዳሚው ዲን የሆኑት ዶ/ር ዳኛቸዉ ንግሩ ተናግረዋል፡፡

ዶ/ር ዳኛቸዉ ባስተላለፉት መልዕክት ባሕር ዳር ከተማ ላይ በተካሄደዉ የእግር ኳስ ውድድር ያስመዘገቡትን አበረታች ዉጤት አጠናከረዉ እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡ ለሁሉም ተወዳዳሪዎች ሙሉ የስፖርት ቱታ ሽልማት በማድረግ ለዚህ ዉድድር እንዲበቁ ላደረጉ የአካዳሚዉ አሰልጣኞች እና መምህራን እንዲሁም ድጋፍ ላደረጉ የዩኒቨርሲቲዉ ከፍተኛ አመራሮች በማመስገን እና መልካም ዉጤት በመመኘት ተጫዋቾችን ሸኝተዋል፡፡

መልካም ዉጤት ለዩኒቨርሲቲዉ የእግርኳስ ክለብ!