ከሰላም ሚኒስቴር ጋር ምክክር ተካሄደ

ባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር የምክክር መድረክ አካሄደ

**************************************************

የባሕርዳር ዩኒቨርሲቲ ከሰላም ሚኒስቴር ጋር በሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት ዙሪያ በፕሬዘዳንት ጽ/ቤት መጋቢት 22/2014ዓ.ም የጋራ ውይይት አካሄደ፡፡

ውይይቱን የመሩት የዩኒቨርሲቲው  አስተዳደር  ጉዳዮች  ተቀዳሚ  ዳይሬክተር  አቶ  ገደፋዉ  ሽፈራዉ እና ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጡት አቶ ንጉሱ ታደሰ ናቸው፡፡

የዩኒቨርሲቲው የተማሪዎች ዲን ዶ/ር ምንይችል ግታው  ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከሌሎች ዩኒቨርሲቲዎች በተለየ መልኩ የተማሪዎችን ሕብረትና የሰላም ፎረም በፓርላማ ደረጃ አዋቅሮ እየሰራ መሆኑን አውስተው  አደረጃጀቱም ለሰላማዊ መማር ማስተማሩ ያለው ፋይዳ የጎላ በመሆኑ አሁን ላይ ባለው ተጨባጭ ሁኒታ ችግር የማይሰማበት ሞዴል የሰላም ዩኒቨርሲቲ መሆኑንን ተናግረዋል፡፡

ዲኑ በማስከተል ለሰላሙ በር ከፋች የሆኑት ሌሎችንም መልካም ተሞክሮዎች እንደ ባሕር ዳር እንደቤቴ (በበዓል ዕለት ከሌላ ቦታ የመጡትን ተማሪዎች በከተማው ውስጥ ባሉ በጎ ፈቃደኛ ቤተሰብ በዓሉን እንዲውሉ የሚደረግበት) ፕሮግራም፣ከተማሪዎች፣ከሰራተኞችና ከከተማው ማህበረሰብ ጋር በሰላሙ ዙሪያ ሰፊ ውይይት በማድረግና በመተማመን የሚሰራው ሰፊ ስራ ተጠናክሮ መቀጠሉ ሰላሙ እንዲሰፍን ማድረጋቸውን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ገደፋውም በበኩላቸው በዩኒቨርሲቲው ፍፁም የሆነ ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እየተከናወነ መሆኑን ገልፀው ሰላም እንዲሰፍን ከሚያደርጉት ነገሮች መካከል በዩኒቨርሲቲው ውስጥ የተጠናከረ የበር ፍተሻ መኖሩ፣ ፌደራል ፖሊስ ተመድቦ እየሰራ መሆኑ፣ተማሪዎች በየግቢያቸው በሰላሙ ዙሪያ እየሰሩ በመሆኑ እና የየግቢዎች አረንጓዴ ልማት መስፋፋት የመሳሰሉት ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመጡት እንግዶች አቶ ንጉሱ ታደሰ እና አቶ ደመቀ ቢያዝን ከዩኒቨርሲቲው ማህበረሰብ የቀረበው ገለፃ ፍፁም ሰላማዊ የመማር ማስተማር ሂደት እየተከናወነ መሆኑን ስለሚያመላክትና ለዚህ ሰላም መስፈን ለተደረገው ጥረት ላቅ ያለ ማስጋና አቅርበዋል፡፡

አቶ ንጉሱ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከአብዛኛው የህብረተሰብ ክፍል ጋር መስራታቸውን ተናግረው በአመዛኙ ከዩኒቨርሲቲዎች ጋር ሰፊ ስራ እንደሚሰሩና አገራዊም ሆነ ብሄራዊ መግባባቶች አስፋላጊ እንደሆኑ በአንክሮ ተናግረዋል፡፡

አክለውም በግቢዎች ውስጥ የሚታዩትን ተግዳሮቶች ከዚያው ሳይወጡ በቶሎ የመፍታት ልምድ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበው የሰላም ፎረሙም በየጊዜው ጠንካራና ደካማ ጉኑን በመመርመር ማስተካከል የሚቻልበትን ሁኔታ ማመቻቸት ለሰላም መስፈኑ ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

አቶ ደመቀም እንደገለፁት ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ብቻ ሳይሆን  በሰላማዊ ቦታም በመገኘት ሰላሙ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚሰራ ተቋም መሆኑን ገልፀው በቅርቡ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ከ1ኛ ክፍል ጀምሮ የግብረ-ገብ ትምህርት እንዲሰጥ የስምምነት ሰነድ መፈራረማቸውን ተናግረዋል፡፡

ታዳሚዎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው የዩኒቨርሲቴው የስራ ኃላፊዎችና የክልሉ የሰላምና ፀጥታ ዘርፍ ኃላፊ ሲሆኑ ሁሉም ሰላማዊ የመማር ማስተማሩ ሰፊ ስራ እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ በዩኒቨርሲቲው የውስጥ ግንኙነት አቶ ግርማው አሸብር አማካኝነት ዩኒቨርሲቲውን የማስተዋወቅ ስራ ተከናውኗል፡፡

 

ዘጋቢ፡- ሙሉጉጃም አንዱዓም