አገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና የደህንነት ጥናት ተቋም "አገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ" በሚል መሪ ቃል የጋራ ጉባኤ አካሄዱ
*************************************************************************
የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲና የደህንነት ጥናት ተቋም (Institute for Security Studies /ISS/) በጋራ በመተባበር አገራዊ ምክክር ለኢትዮጵያ፤አስፈላጊነት ፣ሂደት፣ የባለድርሻ አካላት ሚና እና የቢሆን ትንታኔዎች ላይ ያተኮረ የጋራ ጉባዔ በ22/10/14 በባሕር ዳር ከተማ ኩሪፍቱ ሪዞርትና ስፓ አካሄደ።
የጉባኤውን መከፈት ያበሰሩት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍሬው ተገኘ መረሃ- ግብሩን ላዘጋጁት አካላት ምስጋና እና ከሩቅም ከቅርብም ጉባኤውን ለመታደም ለመጡት ተሳታፊዎችና የፅሁፍ አቅራቢዎች የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክታቸውን አስተላልፈው ጉባኤው ወቅቱን ያማከለ መሆኑንና አገራችን ኢትዮጵያን ካጋጠማት ተግዳሮት ለማውጣት አካታች ብሔራዊ ምክክር ማድረጉ ይበል የሚያሰኝ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ አክለውም አገራችን ኢትዮጵያ የብዝሃ ብሔርና ሐይማኖት ባለፀጋ መሆኗን አውስተው እነዚህ እሴቶች ለዕርስ በርዕስ መግባቢያነት እንዲሁም አንድነት ለማጠናከር የሚያግዙ ቢሆንም ከጊዜ ወደጊዜ የግጭት መንስኤ እየሆኑ በመምጣታቸው አንድነትን ለመፍጠር እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት የሚከሰቱትን የፖለቲካ መካረር ለማለዘብ የጉባኤው ፋይዳ የጎላ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
በተጨማሪም አገራችን ኢትዮጵያ ከገባችበት አዘቅት ለማውጣት የምሁራኑ ሚና ወሳኝ በመሆኑ በጉባኤው ጥልቅ ውይይት እንደሚካሄድና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ ተለይቶ መሬት የነካ ተግባር እንደሚከናወን ፕሬዚዳንቱ መልካም ምኞታቸውን ገልፀዋል፡፡
የጉባኤው ዓላማ የአገራዊ ምክክር ምንነትና ያለውን ጠቀሜታ፣አነሳሽ የሆኑ ገፊ ምክንያቶች እንዲሁም የተሳካ አገራዊ ምክክር በኢትዮጲያ ለማካሄድ ሊሟሉ የሚገባቸው ምቹ ሁኔታዎች ላይ ግንዛቤ ለማስጨበጥ፣ትክክለኛ አካታችና ፍትሃዊ ብሔራዊ ምክክር ተግባራዊ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት ያላቸውን ሚና ማሳወቅ እንዲሁም ምክክሩ ውጤታማ ቢሆን የሚገኘው ሀገራዊ ትርፍ፣ካልሆነ ደግሞ ሊያስከትል የሚችለውን ሀገራዊ ኪሳራ ለማመላከት ነው፡፡
ለምክክሩ መነሻ የሚሆን ፅሁፍ ያቀረቡት ምሁራን ከደህንነት ጥናት ተቋም ዶ/ር ሰሚር የሱፍ
"የአገራዊ ምክክር አስፈላጊነት በታሪካዊ እና ንፅፅራዊ እይታ" በሚል ርዕስ፣ ዶ/ር አደም ካሴ ከ IDEA International ባሉበት ስፍራ በበይነ መረብ "ለተሳካ አገራዊ ምክክር አስፈላጊ ሁኔታዎች በሚል ርዕሰ ጉዳይ፣ በወ/ሮ ሰብለ ሃይሉ "ለአገራዊ ምክክር የባለድርሻ አካላት ሚና" በሚል ርዕስ እና ፕሮፌሰር ሹመት ሲሻኝ "ኢትዮጵያ ከስኬታማ አሊያም ከተሰናከለ አገራዊ ምክክር በኋላ፤ምጥን የቢሆን ትንተናዎች በተሰኘ ርዕስ አቅርበዋል፡፡
በጉባዔው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የተውጣጡ የመንግስት ስራ ኃላፊዎች፣የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ አመራሮች፣መምህራንና ፕሮፌሰሮች እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው የሀይማኖት አባቶች የተገኙ ሲሆን በቀረቡት ፅሁፎች ላይ ሰፊ ውይይት ተካሄዶ ለተነሱት ጥያቄዎች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
የጉባኤውን አንኳር ሀሳቦችና ጎልተው የወጡትን ነጥቦች ያቀረቡት የደህንነት ጥናት ተቋም ተመራማሪና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት አቶ ተግባሩ ያሬድ በአሁኑ ወቅት አገራችን ኢትዮጲያ ጊዜ የማይሰጠው ተግዳሮት እንዳጋጠማትና አገራዊ ምክክር ደግሞ የግጭት ማስተዳደሪያ መሳሪያ ስለሆነ ያለፈውን የታሪክ ትርክት የሚታይበትና የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ የሚለይበት ግንዛቤ መፈጠሩን ገልፀዋል፡፡
በማስከተልም ታሪክ ቀመስ ችግሮችን ምሁራኑ ተረባርቦ በተቋም ደረጃ እንዲሁም የሐይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የተዛባውን አካሄድ በመመለስ የሀገራችንን ህልውና ወደ ነበረበት ሁኔታ ማስተካከል ተገቢ መሆኑ በሰፊው መወሳቱን ተናግረዋል፡፡
የወደፊት የትኩረት አቅጣጫ ሲለይ የተነሱት በርካታ ጉዳዮች ቢሆኑም ለአገራዊ ምክክር "አባይን በጭልፋ" አይነት ስለሆነ በተለይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በስሩ በርካታ ምሁራን ስላሉ ጥበብ በተሞላበት መንገድ አገርን መታደግ እንደሚቻልና ምክክሩ ቀጣይነት እንዲኖረው ፕሮፌሰር ያለው እንዳወቀን ጨምሮ የጉባኤው ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የመዝጊያ ንግግር ያደረጉት የክብር እንግዳው አቶ ክቡር ገና ለፕሮግራሙ አዘጋጆች፣ ለፅሁፍ አቅራቢዎችና ለተሳታፊዎች ምስጋና አቅርበው የሰላሙ ጉዳይ እልባት ያጣው የደከመ ሀሳብ ተሸክመን እየሄድን ስለሆነ ነው ብለዋል፡፡
ለዚህም መፍትሄው ይላሉ በማስከተል አቶ ክቡር አገራዊ ምክክር ሲካሄድ የአሸናፊና የተሸናፊ አይነት ውይይት ሳይሆን ሁሉም በተመሳሳይ አዲስ ሀሳብ ላይ ጥበብ በተሞላበት ሁኔታ መወያየት ከቻለ ዘላቂ መፍትሄ ማምጣት እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡
አቶ ክብሩ አክለውም ምክክሩ የምሁራኑን ሚና አካቶ መቀጠል እንዳለበትና ከታለመው ግብ ለመድረስ ሁሉም ባለ ድርሻ አካላት የበኩላቸውን መወጣት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
 
በሙሉጎጃም አንዱዓለም