አዲስ የሶፍዌር ስልጠና ተሰጠ

ለማኔጂንግ ዳይሬክተሮችና የሰዉ ሀብት ልማት ዳይሬክተሮች አዲስ የሶፍዌር ስልጠና ተሰጠ

በከፍተኛ ትምህርት የመረጃ አያያዝ ስርዓት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ስልጠና በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ለማኔጂንግ እና የሰዉ ሀብት ልማት ዳይሬክተሮች ፔዳ ግቢ በሚገኘዉ የአይሲቲ ስልጠና ማዕከል በአይሲቲ ዳይሬክቶሬትና በበጀትና ልማት ዳይሬክቶሬት ትብብር ተሰጥቷል፡፡

በስልጠናዉ ላይ የመግቢያ ንግግር ያደረጉት የዩኒቨርሲቲዉ በጀትና እቅድ ዳይሬክተር አቶ ሽመልስ በቀለ እንደገለፁት ስልጠናዉ ለአስተዳደር ዘርፉ ለሁለተኛ ጊዜ እየተሰጠ መሆኑን ገልፀዉ ከስልጠናዉ የሚገኙትን መሰረታዊ ጥቅሞች አብራርተዋል፡፡ አቶ ሽመልስ እንዳሉት መረጃዎችን በዚህ ሶፍትዌር ማስቀመጥ ለዉሳኔ ሰጭ አካላት ትክክለኛ መረጃዎችን ለመስጠት ያስችላል፤ እንዲሁም ለድጋፍ፣ ለቁጥጥርና ለሪፖርት ግብዓት ይሆናል ብለዋል፡፡

ስልጠናዉን በማስተባበርና በመስጠት  ላይ የነበሩት የዩኒቨርሲቲዉ የአይሲቲ ዳይሬክተር አቶ ይበልጣል ማሩ በበኩላቸዉ ስልጠናዉ በሀገር አቀፍ ደረጃ በትምህርት ሚኒስቴርና ሌሎች አለም አቀፍ አጋር አካላት በተሰራዉ የዩኒቨርሲቲዎች የመረጃ አያያዝ ስርዓት ላይ የአጠቃቀም ስልጠና መስጠትና ወደ መረጃ ቋቱ የሚገቡ መረጃዎችን እንዲገነዘቡ ማስቻል ነዉ ብለዋል፡፡ አቶ ይበልጣል አክለዉም ስልጠናዉ ባለፉት ሰባት ቀናት ከሌሎች የዩኒቨርሲቲዉ ባለድርሻ አካላት ጋር ሲደረግ እንደነበር ገልፀዉ በቀጣይም ለሚመለከታቸዉ አካላት ይሰጣል ብለዋል፡፡

የስልጠናዉን አላማ አስመልክቶ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ይበልጣል ማሩ ሶፍትዌሩ አጠቃላይ መረጃዎችን በሲስተም በማስገባት በሚፈለጉበት ጊዜ ጥቅም ላይ ለማዋል ያስችላል ብለዋል፡፡

 

ዘጋቢ፦ ሸጋዉ መስፍን