አሸናፊ አሳታፊ የሰብል ዝርያዎች

አሸናፊ አሳታፊ የሰብል ዝርያዎችን የማስፋት ፕሮጀክት አመርቂ ስራ መስራቱ ተገለጸ

*************************************************************************

አሸናፊ አሳታፊ የሰብል ዝርያዎችን የማስፋት ፕሮጀክት (Upscaling Crowdsourced ‘’winner’’ seed varieties project) በፈረንጆች አቆጣጠር ከ2020 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራ ክልል በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ በትግራይ ክልል በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ እና በኦሮሚያ ክልል ሲድ ኢንተርፕራይዝ ጋር በመተባበር አርሶ-አደሩን ተጠቃሚ የሚያደርግ በምርምር የተገኙ የተሻሻሉ እንዲሁም የአካባቢ የሰብል ዝርያዎችን በቀጥታ ብሎም በተዘዋዋሪ ለአርሶ-አደሮች በማዳረስ ቅድመ ስብሰባ እና ድህረ ምርት አየያዝን ጨምሮ ክትትል በማድረግ ውጤታማ ስራ እየተሰራ መሆኑን ተጠቃሚ አርሷደሮች ተናግረዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ የሃገራችን ዋናው የኢኮኖሚ ምሰሶ ለሆነው የግብርናው ዘርፍ ግንባር ቀደም የምርጥ ዘር ተጠቃሚ አርሶ-አደሮች በማምረት ያገኙትን ውጤት ሌሎችም አርሶ-አደሮች እንዲአስተዋዉቁ እና በማካፈል ተጠቃሚ እንዲሆኑ በስፋት መሰራት እና ምርትና ምርታማነትን ለመጨመር፤ በገበያ ተፈላጊና የተሻለ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ለማምረት ግብዓትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ተደራሽነትን እንዲሁም ጥራትን ማረጋገጥ በትኩረት እና አሳታፊ በሆነ መልኩ መስራት እንደሆነ በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል፡፡

ፕሮጀክቱ በደቡብ ጎንደር ዞን ፋርጣ ወረዳ የሀውዘት ቀበሌ፣አዲስ አለም የዘር ብዜት እና ግብይት ማህበር፣ በምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤሊያስ ወረዳ የጥጃ ገጠር ቀበሌ የላቀ ማርቆስ የዘር ብዜት እና ግብይት ህብረት ስራ ማህበር፣ በምዕራብ ጎጃም ዞን ቡሬ ዙሪያ ወረዳ በዋድሪ ቀበሌ ሰርተን እንደግ የዘር ብዜት እና ግብይት ህብረት ስራ ማህበር፣በሜጫ ወረዳ ኩድሚ የዘር ብዜት ማህበር እና ሰሜን አቸፈር ወረዳ ሊበን ዳንጉር ቀበሌ ዘልቆ በመግባት ለአርሶ-አደሩ  የተሻሻሉ የዳጉሳ፣የመኮረኒ ስንዴ እና የባቄላ ምርጥ ዘሮችን በማቅረብ የተሸለ ምርት እንዲመረት ማድረጉ ተገልጿል፡፡   

በባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ መምህር እና ተመራማሪ እንዲሁም የፕሮጀክቱ አስተባባሪ የሆኑት እንደ ዶ/ር ደረጀ አያሌው ገለፃ በአማራ ክልል በስድስት ወረዳዎች የመኮረኒ ስንዴ፣ ባቄላ፣ ቦቆሎ፣ ዳጉሳ እና ሌሎች የተሸሻሉ የሰብል ዝርያዎችን ለአርሶ-አደሮች አድርሷል፡፡ አክለውም ለበርካታ ዓመታት ጠንካራ ስራ በመስራት የቆይታ ጊዜውን ያጠናቀቀው የተቀናጀ የዘር ዘርፍ ልማት (ISSD Ethiopia) ተሞክሮ ያላቸው አርሶ-አደሮችን በማሳተፍ  በአሳታፊ አሸናፊ የሰብል ዝርያዎችን የማስፋት ፕሮጀክት (Upscaling Crowdsourced ‘’winner’’ seed varieties project) ከላይ ከተጠቀሱት የሰብል ዝርያዎች ዉስጥ የባቄላን፤ የመኮረኒ ስንዴን እና የዳጉሳ ዘሮችን ለአርሶ-አደሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በማድረስ እና ለገበሬዎች የህብረት ስራ ማህበራት ስልጠናዎችን በመስጠት የወረዳ የግብርና ባለሙያዎች ጠንካራ የክትትል ስራ ተጨምሮበት በዘንድሮ የሰብል ወቅት በመስክ ምልክታ እንደታየው አመርቂ ውጤት መገኘቱን ዶ/ር ደረጀ ገልፀዋል፡፡ አርሶ-አደሮች ተጠቃሚ ከሆኑባቸው ሰብሎች መካከል  ጉሎ የመኮረኒ ስንዴ በ’’51 አርሷደሮች’’ በዶሻ የባቄላ ዝርያ በ’’107 አርሶ-አደሮች’’ በጃቪ የዳጉሳ ዝርያ በ’’54 አርሶ-አደሮች’’ በሜጫ የዳጉሳ ዝርያ በ’’52 አርሶ-አደሮች’’ እና ነጮ የዳጉሳ ዝርያ በ’’56 አርሶ-አደሮች’’ በአጠቃላይ በስድስቱም ወረዳዎች ላይ 320 አርሶ-አደሮች በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በዚህ ዓመት ተሳታፉ ነበሩ፡፡

በደቡብ ጎንደር ዞነ ፋርጣ ወረዳ የሀውዘት ቀበሌ አርሶ-አደር የሆኑት አቶ አግማሴ ጌጡ እና አቶ የኔዓለም ፀዳሉ በዶሻ የባቄላ እና የመኮረኒ ስንዴ ምርጥ ዘር ተጠቃሚ አርሶ-አደሮች እንዳሉት ከፕሮጀክቱ የተሰጣቸውን ዘር ባገኙት ስልጠና እና በግብርና ባለሙያዎች በመታገዝ የዘሩት የስንዴ እና የባቄላ ሰብል ከጠበቁት በላይ ምርት እንደሚሰጣቸው ተናግረው ፕሮጀክቱ ቀጣይ የተሻሻሉ ምርጥ ዘር በማቅረብ በርካታ ገበሬዎችን የእድሉ ተጠቃሚ በማድረግ አሁን ላይ ያለውን የምርጥ ዘር እጥረት ለመቀነስ የበኩሉን አስተዋፅፆ እንዲያበረክት ጠይቀዋል፡፡ በተመሳሳይም የምስራቅ ጎጃም ዞን ደብረኤሊያስ ወረዳ የጥጃ ጎጠር ቀበሌ የላቀ ማርቆስ የገበሬ ህብረት ስራ ማህበር አርሶ-አደሮች ፕሮጀክቱ ምርጥ ዘር በማቅረብ እና የተለያዩ ሙያዊ ስልጠናዎችን በመስጠት አርሶ-አደሩ በምግብ እህል እራሱን እንዲችል በሚያደርገው የስራ እንቅስቃሴ ደስተኛ መሆናቸውን ገልፀው የተሻሻሉ ተጨማሪ የነጮ ዳጉሳ እና የስንዴ ዝርያዎች እንዲቀርብላቸው አቶ አግማሴ ጌጡ ተናግረዋል፡፡

አሸናፊ አሳታፊ የሰብል ዝርያዎችን የማስፋት ፕሮጀክትን (Upscaling Crowdsourced ‘’winner’’ seed varieties project) ወክለው በመስክ ምልከታው ላይ የተሳተፉት ዶ/ር ሀይሉ ተፈራ ካሁን በፊት ይታዩ የነበሩ የዘር እጥረትን እና ብክነትን በመቅረፍ እና በአንድ ጊዜ በርካታ አርሶ-አደሮችን ተጠቃሚ ለማድረግ የተሰራውን ስራ አድንቀዋል፡፡ ይህ በእርግጥም የአሸናፊዎችን ዝርያዎች የበለጠ ለማስፋት እና የፕሮጀክት ግቦችን ለማሳካት፣ በዘር እራስን መቻል በቅርብ ጊዜ ለማረጋገጥ እና ለኢንዱስትሪዎች እና ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የምርት ደረጃ ውስጥ ለመግባት ጥሩ አጋጣሚ ይፈጥራል ሲሉ ተናግረዋል። ዶ/ር ሃይሉ አክለውም ይህ ለተመራማሪዎች፣ የፕሮጀክት ስራ አስኪሃጆች እና የኤክስቴንሽን ባለሙያዎች አርሶ-አደሮቻች የምግብ እና የተመጣጠነ ምግብ ዋስትና እንዲያገኙ ቁርጠኝነትን በተላበሰ መንፈስ ከበፊቱ የበለጠ ጠንክረው እንዲሰሩ እስካሁን ለሰሩት ስራ እውቅና መስጠት ተገቢ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሰራተኞቹ ጠንክረው መሥራታቸውን እንደሚቀጥሉ እና የታለሙትን ዓላማዎች እንደሚያሳኩ ተስፋ እንዳላቸው ተናግረዋል።