ችግኝ ተከላ

               ችግኝ ተከላ በብር አዳማ

ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የተመረጡ ተራራማ ቦታዎችን በደን ለመሸፈን የችግኝ ተከላ አከናወነ፡፡

በምዕራብ ጎጃም ዞን ይልማና ዴንሳ፣ ቋሪት፣ እና ሰከላ ወረዳዎች የሚገኙ የተራቆቱ ተራራማ ቦታዎች መልሰው እንዲያገግሙ ለማድረግ በጥናት ተመርኩዞ ሀገር በቀል በሆኑ ችግኞች ለመሸፈን ዩኒቨርሲቲው ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ ተነገረ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ስር በሚገኘው የብር አዳማ ተፋሰስ ልማት ፕሮጀክት ዙሪያ የአካባቢውን ማህበረሰብ በማስተባበር  የችግኝ ተክላ እና ግንዛቤ ፈጠራ ስራ ተካሂዷል፡፡

ከፕሮግራሙ በኋላ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት የብር አዳማ ተፋሰስ ልማት አስተባባሪ አቶ ደመቀ ላቀው እንደተናገሩት ዩኒቨርስቲው የአካባቢውን ስነ-ምህዳር ወደ ነበረበት ለመመለስ የችግኝ ጣቢያዎችን የማቋቋም፣ የችግኝ ተከላ እና በችግኝ የተሸፈኑ ተፋሰሶችን ከሰው እና ከእንስሳ ንክኪ ነፃ የማድረግ ስራ እየሰራ  መሆኑን ተናግረዋል፡፡  ይህን የመሰለውን የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃና ክብካቤ ስራ ውጤታማ ለማድረግ ከአካባቢው ነዋሪዎች የተሸለ አካል ባለመኖሩ ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራው ትኩረት እንደሚሰጠው  ተጠቁሟል፡፡