ትላልቅ የድንች ዘርን ከታትፎ በማከም መዝራት

ትላልቅ የድንች ዘርን ከታትፎ በማከም መዝራት የድንች ምርትን እንደሚያሳድግ ተጠቃሚ አርሶ አደሮች ተናገሩ

(ሰኔ 29/2014 ዓ.ም፣ ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-BDU) የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ለድንች ምርት ምቹ በሆነው የይልማና ዴንሳ፣ ቋሪት እና ሰከላ አዋሳኝ በሆነው ብር አዳማ አካባቢ ለሚኖሩ አርሶ አደሮች ትላልቅ የድንች ዘርን ከታትፎ በማከም መዝራትና የድንችን አበባ በመቀንጠብ የድንች ምርት የመጨመር እና ዘርን የመቆጠብ  ቴክኖሎጂን አስመልክቶ ስልጠናውን ወሰደው ማሳቸውን በዘር የሸፈኑ አርሶ አደሮችን ማሳ በዩኒቨርሲቲው የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ነፃነት በየሮ የተመራ የባለሙያዎች ቡድን ምልከታ አድርጓል፡፡

በመስክ ምልከታው ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶ/ር ነፃነት በየሮ እንዳሉት የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ከመማር ማስተማር ጎን ለጎን የህብረተሰቡን ችግር ሊፈታ የሚችል የምርምር እና ማህበረሰብ አገልግሎት ስራዎችን እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በቋሪትና  በይልማና ዴንሳ ወረዳዎች በፈንገጣ፣ በስም አረጋ እና ብር አዳማን ጨምሮ በሌሎችም ቀበሌዎች ከተፈጥሮ ሐብት ጥበቃ ጀምሮ የወተት ምርትን ሊጨምሩ የሚችሉ የላሞችን እና በጎችን ዝርያ የማሻሻል፣ ትምህርት ቤቶችን የመደገፍ እና ለአርሶ አደሩ ነፃ የህግ አገልግሎት የመስጠት ስራዎችን በስፋት እየሰራ እንዳለ በመስክ ምልከታው ላይ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ  ትላልቅ  የድንች ዘርን  በመከታተፍ መዝራትና የድንችን አበባ በመቀንጠብ ምርት እና ምርታማነትን የመጨመር ቴክኖሎጂን አስመልክቶ  ስልጠና የወሰዱ አርሶ አደሮች የወሰዱትን ስልጠና በጥሩ ሁኔታ በመተግበራቸው በማሳቸው ላይ የተሻለ  የድንች ሰብል በማየታቸው መደሰታቸውን ተናግረው ሌሎች የአካቢው አርሶ አደር ቴክኖሌጅውን በስፋት በመጠቀም የድንች ምርትን  ማሳደግ እንደለባቸው ተናግረዋል፡፡

በይልማና ዴንሳ ወረዳ የስም አረጋ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አርሶ አደር ቻሌ አለሙ እና በቋሪት ወረዳ ፈንገጣ ቀበሌ ነዋሪ እና የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ  የሆኑት አርሶ አደር ሞላ አዘነ እንዳሉት አካባቢው በከፍተኛ ደረጃ ድንች አምራች በመሆኑ አርሶ አደሩ ካለው መሬት ላይ ሃምሳ በመቶውን በድንች ሰብል ስለሚሸፍን የዘር እጥረት እንደሚያጋጥማቸው ተናግረዋል፡፡ አሁን ላይ ግን የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ ያመጣውን  ቴክኖሎጂ ተጠቅመን ትላልቅ የድንች ዘርን በመከታተፍ እና በማከም ዘርተው የዘር እጥረቱን ማስቀረት መቻላቸውን ተናግረው  አበባውን በመቀንጠብ ምርቱን እንዲጨምር የማሳ እንክብካቤ በማድረግ የዘሩት ዘር በሙሉ በማሳው ላይ በማየታቸው የሚሰጠውን ውጤት በጉጉት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል፡፡ ሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች ቴክኖሎጂውን ለመጠቀም ከፍተኛ ተነሳሽነት አንዳሳደረባቸው ተጠቀሚ አርሶ አደሮች አክለው ተናግረዋል፡፡

ከመስክ ምልከታው በኋላ አርሶ አደሮች በትግበራው ወቅት ያጋጠሟቸውን ችግሮች እና ሌሎች አርሶ አደሮች የቴክኖሎጂው ተጠቃሚ ለመሆን የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች መሰርት አድርጎ ውይይት ተደርጓል፡፡ በመስክ ምልከታው ላይ የባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ግርማው አሽብርን ጨምሮ በማሕበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ስር የሚሰሩ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል፡፡

ባሕር ዳር ዩኒቨርሲቲ-ባዳዩ-BDU

ከዓባይ ጓዳ ጥበብ ሲቀዳ

Wisdom at the source of Blue Nile

Thank YOU for visiting and inviting our pages, for your likes and shares!

ለተጨማሪ መረጃዎች፡-

Telegram ፡- t.me/BDU_ISC_Official

Facebook: - https://www.facebook.com/bduethiopia

YouTube ፡- www.youtube.com/c/BduEduEt

LinkedIn ፡- www.linkedin.com/school/bahir-dar-university

Twitter: - https://twitter.com/bdueduet

Tiktok:- https://vm.tiktok.com/ZMLgRxdfL

website :- www.bdu.edu.et